የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀመር በስሌትም ሆነ በትርጉም የተለየ ነው - መጋቤ ሃዲስ ስቡህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀመር በስሌትም ሆነ በትርጉም የተለየ ነው - መጋቤ ሃዲስ ስቡህ

አዲስ አበባ ጷጉሜ 4/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀመር በሌላው ዓለም ከሚተገበረው አቆጣጠር በስሌትም ሆነ በትርጉም የተለየ እንደሆነ ምሁሩ ገለጹ።
የጁሊያን ብሎም የጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመሮች እምነትን ሳይሆን ታሪክን ታሳቢ ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያ በአንድ ዘመን ውስጥ የሚገኙ ወራት የየራሳቸውን ትርጓሜ ይዘዋል።
መጋቢ ሃዲስ ስቡህ አዳምጤ ይባላሉ። በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአንድምታ ትርጓሜ መምህር ናቸው። እንደ እሳቸው ኢትዮጵያ ከብሉይ ዘመን በፊት አመታትን ትቆጥር ነበር።
የዘመን አቆጣጠር (ባህረ ሃሳብ) ቁጥር ያለው ዘመን በሚል ትርጉም ይታወቃል ይላሉ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ።
‘ባህረ ሃሳብ’ እንደ ስያሜው ትንታኔው ጥልቅና ምስጢሩም የረቀቀ እንደሆነ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት ይናገራሉ በማለትም ያብራራሉ።
በዚህ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ቀመር /ስሌት እንደሚገኝ አመልክተዋል።
እንደ መጋቤ ሃዲስ የኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ከጁሊያንም ሆነ ከጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በጣም የተለየ ነው።
በዓመቱ ውስጥ ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚከሰቱ ወራትም የየራሳቸውን የሁኔታ ትርጓሜ በመያዝም አገሪቱ ከሌሎች የተለየች ሆና እንድትታይ አድርገዋታል።
የቀናት ብዛት ከወር ቀርቶ ከሳምንትም አንሶ የሚታይባት ወርሃ ጳጉሜን ትርጓሜዋ የሆነችውን ያሳብቅባታል።
ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት የፊታችን ዓርብ ትቀበላለች።