አገር ያለ ንግዱ ማህበረሰብ አይገነባም --- አቶ ጃንጥራር አባይ

አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2012 (ኢዜአ) አገር ያለ ንግዱ ማህበረሰብ ንቁ ተሳትፎ አይገነባም ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ጳጉሜን 4- “የምስጋና ቀንን” አስመልክቶ የንግዱ ማህበረሰብን የማክበር እና የማመስገን መርሃግብር ዛሬ አከናውኗል።   

በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት አቶ ጃንጥራር አባይ የንግዱ ማህበረሰብ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ህሊናው የፈቀደውን አስተዋጽኦ በበጎነት ሲያበረክት በመቆየቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አገር ያለ ንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎ እንደማይገነባም ተናግረዋል፡፡

"በአገሪቱና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የንግድ ማህበረሰብ አባላት የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን በማሳደግ በኢትዮጵያ ሥራዎች እንዲስፋፉና እንዲቀላጠፉ የሚያደርጉት ድጋፍ የላቀ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የንግዱ ማህበረስብ የጀመረውን መልካም ተግባር በቀጣይ ዓመትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተከሰተውን የአቅርቦት እና የስርጭት ተግዳሮት በማቃለል ህብረተሰቡ የፈለገውን አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረጋቸው ምስጋና ችረዋቸዋል።

አቶ መላኩ የንግድ እንቅስቃሴ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት፣ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት እና ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥበት ዘርፍ በመሆኑ እንደ አገር "ንግድ የደም ስር ነው”  የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ተናግዋል።

በዛሬው ዕለት ምስጋና የተቸራቸው ነጋዴዎች የንግድ ህግና ስርዓት ያከበሩ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭምሪ ያላደረጉ፣ ጥራት ያለው ምርት ለሸማቾች ያቀረቡ እንዲሁም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተዳረጉ ዜጎች ድጋፍ እና የማዕድ ማጋራት ተግባር ያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ ዩሱፍ ናቸው።

እንደ ኃላፊው ገለጻ እውቅናው ምስጉን ነጋዴዎቹ በጎ ተግባራቸውን ወደፊትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከማድረግ ባለፈ ሌሎች ነጋዴዎች የእነርሱን ፈለግ ተከትለው በመልካም ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ያነሳሳል።

እውቅና ካገኙት መካከል የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ፎረም ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘሀራ መሀመድ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ ለተሰጣቸው እውቅና ምስጋና አቅርበው፣  በቀጣይ ለምስጋና ያበቃቸውን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ጳጉሜን አራት-የምስጋና ቀን “የምናመሰግነው ስለሚገባችሁ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም