የኢትዮጵያ መንግስት ታሪካዊ የለውጥ ሂደት እያካሄደ ነው - በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት ታሪካዊ የለውጥ ሂደት እያካሄደ ነው - በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር
አዲስ አበባ ሃምሌ 6/2010 የኢትዮጵያ መንግስት ታሪካዊ የለውጥ ሂደት እያካሄደ መሆኑን በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ገለፁ። በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡሉሶይ በኢትዮጵያና በቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነትና በቱርክ የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የከሸፈበት ሁለተኛ ዓመት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። አምበሳደር ኡሉሶይ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አዲሱ አመራር የሚደነቅ ታሪካዊ የለውጥ ሂደት እያከናወነ ነው። በአገሪቷ እየተከናወኑ ያሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደቶችና የዴፕሎማሲ ሥራዎችን አድንቀዋል። በተለይ ከኤርትራ ጋር የቆየውን አለመግባባት ለመፍታት የተከናወነውን ሥራ "ጠንካራ የዴፕሎማሲ ስኬት" ብለውታል። "የቱርክ ህዝብና መንግስት ይሄን ለውጥ ይደግፋሉ" ያሉት አምባሳደሩ፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። ከቀናት በፊት የቱርክ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ የተጀመረውን ዕርቀ ሰላም አገሪቷ እንደምትደግፍ መግለፁ ይታወሳል። ዕርቀ ሰላሙና በሁለቱም አገሮች መሪዎች መካከል የተደረገው ስምምነት ለአገሮቹ ዕድገትና ብልፅግና እንደሚጠቅምም ገልጿል። ከዚያ ባሻገርም በአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ ሰላምና ጠንካራ ትብብር ለመፍጠርም እንደሚያስችል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ያለውን እምነት አመላክቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን አምባሳደር ፋቲህ ኡሉሶይ ከሁለት ዓመት በፊት በቱርክ የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የከሸፈበት ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክተውም ማብራሪያ ሰጥተዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት የተሞከረውና የከሸፈው መፈንቅለ መንግስት አቀናባሪ ተብሎ የሚታሰበው በፈቱላህ ጉሌን የሚመራው ድርጅት ላይ በመዋቅሩና የአፈጻጸም ሂደቱ ላይ የሚደረገው ምርመራ እስካሁን መቀጠሉንም ተናግረዋል።