ቀጥታ፡

የቅዱስ ላልይበላ የቅርስና ቱሪዝም ጥናት ተቋም አገራዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ሚናው ጉልህ ነው ተባለ

 አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2012 (ኢዜአ)

የቅርስና ቱሪዝም ጥናት ተቋም በላልይበላ ከተማ መቋቋሙ ዘርፈ ብዙ አደጋ የተጋረጠባቸውን አገራዊ ቅርሶች ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተጠቆመ።

ሰሞኑን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለቅዱስ ላልይበላ የቅርስና ቱሪዝም ጥናት ተቋም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።


የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ የቀደምት የጠቢባንና ሳይንሳዊ ዕውቀቶች ባለቤት በመሆኗ ነባሩን አገራዊ ዕውቀት በትውልዱ ላይ መስራት ይጠይቃል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ወደ ሁለንተናዊ ብልጽገና ለመሸጋገር ነባሩን የሳይንስ ፍልስፍና ቀመር ይዞ ዕውቀትን ለትውልድ ማሸጋገር ይገባል።

ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ከኢትዮጵያ ቀደምት የጥበብ አሻራዎች መካከል አንዱ በሆነው በደብረ ሮሀ ቅዱስ ላልይበላ ታሪካዊ ቅርሶች አቅራቢያ ተቋሙመከፈቱ ነባሩን ዕውቀት ለማሸጋገር ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው በበኩላቸው፣ ዛሬ ድረስ ለዓለም ትንግርት የሆኑ ኪነ ህንጻዎችን የገነቡ ሰዎች የልጅ ልጆች መሰል ቅርሶችን ለመገንባት ብቻ ሳይሆን ለመጠገን ከዕውቅት መራቃቸውን አስታውሰዋል።

ይህም ነባሩ አገራዊ ጥበብ ላይ ባለመሰራቱና ለትውልድ ባለመሸጋገሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስር የተከፈተው የቅዱስ ላልይበላ የቅርስና ቱሪዝም ጥናት ተቋም ቀደምት አገራዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ የቱሪዝም ስፍራዎችን ለማልማት የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት እንዲሁም አዳዲስ የጥበብ አሻራዎችን ለማሳረፍ እንደሚያገዝ ገልጸዋል።

ይህም የራስን ሀብት በራስ አቅም ለመጠበቅ ሚና እንደሚኖረው ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።

የሰሜን ወሎና ከሚሴ ሐገረ ሰብከቶች ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በቅርሶች ላይ የሚሰራ የትምህርት ተቋሙ መከፈቱ ለአካባቢው ነዋሪ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች በሕመምና በሞት አፋፍ ላይ እንደሆኑ ገልጸው፣ የሰው ልጆች ሲታመሙ ኃኪም እንደሚሹ ሁሉ ቅርሶችም የሚንከባከባቸው የሰው ኃይል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የሚገነባው የትምህርት ተቋም በርካታ ዘመናትን ያስቆጠሩ የላስታ ላልይበላ አካባቢ ቅርሶችን ከጥፋት ለመታደግና ለትውልድ ለማሸጋገር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

"በትምህርት ተቋሙ ተምረው ከሚመረቁ ተማሪዎችም በሙታን ቅርሶችን ለማጠናት፣ ህሙማን ቅርሶችን ለማከም ብሎም ሕያዋን ቅርሶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ጥበብ መጨበጥ ይገባቸዋል" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም