የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአካባቢያዊ አጀንዳዎች ይልቅ ለብሔራዊ መግባባት መስራት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአካባቢያዊ አጀንዳዎች ይልቅ ለብሔራዊ መግባባት መስራት ይገባቸዋል
አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2012 (ኢዜአ) ፖለቲካ ፓርቲዎች ከአካባቢያዊ አጀንዳዎች ይልቅ ብሔራዊ መግባባት በሚፈጥሩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገለጹ።
ኢትዮጵያ አዲስ ዓመትን ለመቀበል የቀናት ዕድሜ የቀራት ሲሆን አገሪቷ በ2012 ዓ.ም በፖለቲካው መስክ የተለያዩ ሁነቶችን አስተናግዳለች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ሽልማት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድርና የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ግጭቶችና አለመረጋጋት እንዲሁም የሰዎች መፈናቀል፣ ሞትና ንብረት መውደም በዓመቱ የታዩ አበይት ክስተቶች ነበሩ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) መስራች የሆኑት ፖለቲከኛ አቶ ተሻለ ሰብሮ ኢትዮጵያ እየተገባደደ ባለው ዓመት መልካምና ጥሩ የማይባሉ ክስተቶችን ማስተናገዷን ይገልጻሉ።
"በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች ምክንያት በንጹሀን ዜጎች ላይ የደረሰው ሞትና የንብረት መውደም እጅግ አሳዛኝ የነበረ ክስተት ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶችም ዜጎች ከቄያቸው ከመፈናቀላቸው ባለፈ በአጠቃላይ የነበረው አለመረጋጋት የኢትዮጵያን ህልውና መፈታተኑን ተናግረዋል።
ከነበሩት ፈተናዎች አንጻር በጋራ ሆኖ ኢትዮጵያን ማስቀጠል መቻሉ የዓመቱ ትልቁ ስኬት እንደሆነም ነው አቶ ተሻለ የገለጹት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት፣ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም የተወሰዱ እርምጃዎች መልካም የሚባሉ እንደሆነም አመልክተዋል።
በ2013 ዓ.ም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከራሳቸው አካባቢያዊ አጀንዳ ወጥተው ብሔራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አቶ ተሻለ ገልጸዋል።
አቶ ተሻለ እንዳሉት ዜጎች ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንታዊነት ላይ ተመስርተው ያላቸውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፤ የጥፋት ኃይሎችን አጀንዳ ሊቀበሉም አይገባም።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባቸው ያመለከቱት ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው።
በ2013 ዓ.ም ግጭቶች ቀንሰው ኢትዮጵያ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንድትደረስ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው "በአዲሱ ዓመት በተለይ ወጣቶች አገራቸውንና ህዝባቸውን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።
የፖለቲካ ተዋናዮች በአጠቃላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ጥቅም በማስጠበቅ ለአገራዊ እድገት በጋራ መቆም እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ፓለቲከኞቹ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታ፣ የብልጽግና እና የስኬት እንዲሆን ተመኝተዋል።