የ2012 ዓበይት ክንውኖች

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን3/ 2012(ኢዜአ) የ2012 መስከረም ሲጠባ ሁለት አበይት ጉዳዮች ፈር ይዘዋል።

አንደኛው በ40 ሄክታር መሬት ላይ ባረፈዉ ታላቁ ቤተ-መንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው የአንድነት ፓርክ ለህዝብ ክፍት መሆን ሲሆን፣ በታላ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብን የውኃ አሞላል በተመለከተ ግብፅ ያቀረበችው ሀሳብ የኢትዮጵያ መንግስት እንደማይቀበለውና እንደማይደራደርበት አስታውቋል።

በወቅቱ ግብጽ ያቀረበችው ሃሳብ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ እንድትለቅና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ ዋና ስራው ውሃ መልቀቅ ብቻ እንዲሆን የሚጠይቅ ነበር።

ይህም በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የተፈረመውን የአባይ ውሃ አጠቃቀም የመርህ ስምምነት ነው።

በወርሃ ጥቅምት ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት በወሰዷቸው እርምጃዎችና በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሁለት አስርታት የዘለቀውን የሻከረ ግንኙነት ወደ ሰላማዊ ግንኙነት ለመቀየር ባደረጉት ጥረትጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የ2019(እንደ አውሮፓያን አቆጣጠር) የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

በዚሁ ወር ውስጥ ኢትዮጵያ የኒዩሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ማዋል የምትችልበትን መደበኛ ስምምነት ከሩሲያ ጋር ተፈራርማለች።

በህዳር ወር ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት በስተቀር) ውህደቱን በሙሉ ድምጽ አጸድቆ አጋር ይባሉ የነበሩ ፓርቲዎችን በማካተት የብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሰረተ።

የሲዳማ ዞን ህዝቦች ያቀረቡት የክልልነት ጥያቄን ለመመለስ ህዝበ ውሳኔ ተካሄደውም በዚሁ ወር ነበር።

የሽብር ወንጀል መከላከልና መቆጣጠሪያ ዓዋጅ የጸደቀበት ወርሃ ታህሳስ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳተላይቷን ወደ ህዋ አመጠቀች። 'ETRSS-1' የተሰኘችው ምድርን እየቃኘችና በፎቶ እየመዘገበች መረጃ የምትሰበስበው ይህች ሳተላይት የኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ መጀመሩን የምታበስር ናት።

ጥር የተለያየ ሁነትን ያስተናገደ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህዳር ወር ውህደት መፍጠሩን ያስታወቀውን ኢህአዴግ ሶስት አባል ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመሥረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሠራረት ከሚያሳየው መዝገብ መረዳቱን በመጠቆም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን በሙሉ ድምፅ የወሰነበት አንዱ ሁነት ነው።

254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የገናሌ ዳዋ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተመረቀው በዚሁ ወር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉትም በዚህ ወር ሲሆን፣ በቆይታቸው በአገሪቱ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል።

የዓመቱ አጋማሽ ወርሃ የካቲት ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

የአካባቢ ደህንነትን ለመጠበቅ ሲባል ከተወሰነ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመገደብ እንዲሁም ለጤና ጎጂ በሆኑ ምርቶች ላይ ያለውን የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔን በመፈተሽ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ያጸደቀው በየካቲት ወር ላይ ነው።

ዓለምን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የከተተው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ በታወቀበት መጋቢት ወር በርካታ ሁነቶች ተከናውነዋል።ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወሰደችው የጥንቃቄ ርምጃ በርካታ አድናቆትን ያገኘ ነበር።

አገራዊ ምርጫ በዓመቱ ለማካሄድ ዝግጅት ስታደርግ የነበረችው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወረርሽኙ ጫና የተነሳ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካሄድ አለመቻሉን አስታውቋል።

በዚሁ ወር ኢትዮጵያ የግድቡ አፈጻጸም 72 በመቶ ማድረሷን ተከትሎ ግድቡን በውሃ ለመሙላት የምትከተላቸውን ምዕራፎችና የአሞላል ሒደቶች የተመለከተ አቋሟን ይፋ አድርጋለች።

በሚያዚያ ወር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲደረግ ወስኖ የላከውን ረቂቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጽድቆታል።

የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሮች ተቋማት የሚመሩበት የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ወጥቶ ስራ ላይ የዋለው በሚያዝያ ወር ነበር።

መንግስት ለኢኮኖሚው መረጋጋት ሲባል በሕክምናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ተመጣጣኝ የመከላከል ዕርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ያስታወቀው ሚያዚያ ላይ ነበር።

በግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዓመቱን አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በሀዋሳ ከተማ አስጀምረዋል።

ሰኔ በርካታ ሁነቶች ተከናውነውበታል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበለት የሕገ -መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ የወሰነው በዚህ ወር ነበር።

ምክር ቤቱ ከሕገ -መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ መሰረት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ሥጋት ሆኖ ባለበትና የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀንቶ በሚቆይባቸው ጊዜያትና ከተነሳም በኋላ ምርጫ ተካሂዶ የሥልጣን ርክክብ እስኪፈጸም ድረስ የሕዝብ ተወካዮች፣ የፌዴሬሽን የክልል ምክር ቤቶች በተጨማሪም የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲቀጥል ወስኗል።

በወርሃ ህዳር በህዝበ ውሳኔ ምላሽ ያገኘው የሲዳማ ክልል ከነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጋር የሥልጣን ርክክብ አድርጓል።

ከለውጡ በፊት 2 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር የነበረው የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በተያዘው ዓመት ወደ 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር ማደጉ ተገልጿል።

በተለያዩ ጊዜያት ብሔርን ከብሔር ጋር በማጋጨት ተጠርጥረዋል በተባሉ ሦስት የመገኛ ብዙኃን ላይ መንግስት አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ፣ በጡረታ ለተሰናበቱ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የተፈቀደው ልዩ ጥቅማ ጥቅም ቀሪ እንዲሆን ማድረግ፣ ግብፅ ድርድሩ የውኃ ክፍፍል ላይ እንዲሆን አቋም በመያዟ መግባባት አለመቻሉን ኢትዮጵያ ለፀጥታው ምክር ቤት ማስታወቋ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው የሳይበር ጥቃት መክሸፉ የተገለጸውም በዚሁ ወር ነበር።

በወርሃ ሐምሌ የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የተገለጸበት ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሃሴትያደረጉበት ወር ነበር።

ኢትዮ-ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት 47 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል።

በሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ያለው አገር አቀፍ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በይፋ ተጀምሯል።

በነሐሴ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአንድ ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በሱዳን አድርገው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የሚያጠናክር ሥራ ሰርተዋል።

በሶስቱ ተፋሰስ አገሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በድርድር ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ወደ ተቋረጠው ድርድር በመመለስ የጋራ መፍትሔ እንዲደረስ መወሰኗን ሱዳን አስታውቃለች።

ለሱዳን የለውጥ ጉዞ የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃ ተቋማት ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርንና ሽብርተኝነትን በጋራ በመከላከል እንዲሁም በድንበር አካባቢዎች የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ያደረጉት በነሐሴ ውስጥ ነው።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ፣ በምጣኔ ሀብት የዲፕሎማሲ ስራም ከ200 በላይ አለም አቀፍ ድርጅቶችና አልሚዎች መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ ቅድመ ስምምነት ማድረግ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደትም በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሀሳብም ትልቅ ተጽእኖ የፈጠሩበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለ10 ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሹመት መስጠት እንዲሁም ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው መሾም የወሩ ክስተቶች ነበሩ።

የእንጦጦ ና የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ ክፍት ሲሆኑ የ''ገበታ ለሃገር'' መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በመጀመሪያ ዙር ለመረጣቸው አምስት ፕሮጀክቶች ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ ሳኒታይዘርና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ማምረት ጀምሯል።

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2012 በጀት ዓመት 233 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን በዚሁ ወር አስታውቋል።

ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ የ5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ከታሰበለት ጊዜ ቀድሞ መጠናቀቁም የተገለጸው በዚሁ ወር ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ እና ሌሎችከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ መግባባት ላይ ውይይት አድርገዋል። 

የቤቶች ኮርፖሬሽን በመዲናዋ ለሚያስገነባው ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ስምምነት ተፈራርሟል።

ዓመቱ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ ስኬት ማስመዝገብ የተቻለበትና ለ2013 መሰረት የሚሆኑ በርካታ ስራዎች የተሰሩበት ሆኖ አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም