በደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ
ደሴ፣ ጻጉሜ 3/2012(ኢዜአ) በደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለችግር ለተጋለጡ ሁለት ሺህ 400 ሰዎች ለአዲስ ዓመት በዓል መዋያ የሚሆን የምግብ እህልና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
ደሴ ኢዜአ ጻጉሜ 3/2012 በደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለችግር ለተጋለጡ ሁለት ሺህ 400 ሰዎች ለአዲስ ዓመት በዓል መዋያ የሚሆን የምግብ እህልና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ እሸቱ እንደገለጹት በኮሮና መከሰት ምክንያት ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ለችግር መጋለጣቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
ችግሩ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል የአዲስ ዓመት በዓልን በደስታ እንዲያከብሩ ለማድረግ ለሁለት ሺህ 100 አቅመ ደካሞች የምግብ እህልና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
“ከድጋፉ መካከል 277 ኩንታል ዱቄት፤ 25 ኩንታል መኮረኒ፤ 254 ካርቶን ፓስታ፤ ከሁለት ሺህ በላይ የተለያየ ሳሙና ሌሎችም ይገኙበታል” ብለዋል፡፡
ድጋፉ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የተገኘ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው እንደሆነም ገልፀዋል።
የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አይቸሽ ከድር በበኩላቸው ከዚህ በፊት በቀን ስራ የሚተዳደሩ ቢሆንም አሁን ስራ በመጥፋቱ ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የተደረገላቸው 25 ኪሎ ግራም ዱቄትና ሌሎች ቁሳቁሶች የእለት ችግራቸውን ለመቋቋም እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል።
ሌላዋ የሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘቢባ መሃመድ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስራ በመጥፋቱ አራት ቤተሰብ ይዘው በባዶ በቤት ተቀምጠው እንደነበረ ገልጸዋል።
የተደረገላቸው ድጋፍም የዕለት ችግራቸውን ያለለላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን አስረድተዋል።
በደሴ ከተማ አስተዳደር ኮረና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያየ የምግብ እህል መሰብሰቡ ታውቋል።
በተመሳሳይ ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅቶች በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት 636 ሸህ ብር ግምት ያለዉ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን በድርጅቱ የደብረ ብርሃን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታነህ በዛወረቅ አስታውቀዋል።
ድጋፉም ደብረሲና እና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለሚኖሩ 300 ችግረኛ ወገኖች መሆኑንም ገልጸዋል።
“ዛሬ የተደረገው ድጋፍ በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሰዎች አዲሱን ዓመት ተደስተው እንዲውሉ ለማድረግ በማሰብ የተከናወነ ነው” ብለዋል።
በድጋፉም ለእያንዳንዱ ግለሰብ 50 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ 3 ሊትር የምግብ ዘይት፣ 10 ኪሎ ግራም ሩዝና የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ይገኙበታል።
የደብረ ብርሀን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መርከብ ለማ “ድርጅቱ ኮሮናን በመከላከል እያደረገ ያለው የምግብ አቅርቦትና ሌሎች ድጋፎች ከህዝብ ጎን መቆሙን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ 5 ሚሊየን ብር መድቦ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው፤ በቀጣይ የምግብ እህል እና የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ለሚያስፈልጋቸዉ ህፃናትም ድጋፍ ለማድረግ የመለየት ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የተደረገላቸው ድጋፍ ወቅታዊ ችግሮችን ተቋቁሞ ለመዝለቅ ያግዛል ያሉት ደግሞ በደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ብዙአየሁ ተስፋዬ ናቸው።
“ዛሬ በድርጅቱ የተደረገላቸው የምግብ እህል ድጋፍ ለጊዜው እፎይታ ከመስጠቱም በላይ የዘመን መለወጫ በዓልን በደስታ ለማሳለፍ ያግዘኛል” ብለዋል።
የአዲስ ዓመት በዓል መግቢያንና በኮሮና መከሰት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ጫና ያሰደራባቸውን ሰዎች የመደገፍ ስራ በየከተሞች እየተከናወነ ይገኛል።