ቀጥታ፡

በልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ መሥራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዳማ፣ ጷጉሜን 03/2012 (ኢዜአ) በኢንቨስትመንትና የልማት ፕሮጀክቶች ሊኖር የሚችለውን አካባቢያዊና ማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ መሥራት እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የ2012 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ አሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ዙሪያ በአዳማ ከተማ በባለደርሻ አካላት እያስገመገመ ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መለስ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሚሽኑ በኢንቨስትመንትና የልማት ፕሮጀክቶች ዘንድ ሊኖር የሚችለውን አካባቢያዊና ማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ መሥራት አለበት።

መሪ ዕቅዱ አሁን የሚታየውን የልማት ፕሮጀክቶችና የኢንቨስትመንት ተቋማት አካባቢያዊና ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖን በዘላቂነት ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይ ባለፉት ዓመታት የነበሩ የሕግ ማዕቀፎች ክፍተት እንዳለባቸው ያመለከቱት ሰብሳቢዋ የሚሰራው ግምገማው ይህን ክፍተት በመሙላት በዘርፉ  የተሻለ  ልማት ማከናወን የሚያስችል ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተፋሰስና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ገልጸው በእርከን ሥራና ተፋሰስ ልማት ጥሩ ተሞክሮና ውጤት ቢመጣም የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብና ከማሳደግ አኳያ ክፍተት መኖሩንም ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ለደን ልማት መሠረት የሆኑ የአረንጓዴ አሻራ መረሀ ግብር ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በሥነ ሕይታዊ ሥራ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው ዕቅዱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው በአካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ሥራ ላይ ለሀገሪቱ የደን ልማትና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ መሠረት የሚሆኑትን በዘላቂነት ለማከናወን  ነው ብለዋል።

የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የተራቆቱትን በደን ለመሸፈን የአረንጓዴ አሻራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፤ ኅብረተሰቡን በባለቤትነት ለማሳተፍና ተጠቃሚ ለማድረግ ጭምር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አሁን በልማት ፕሮጄክቶችና የኢንቨትመንት ተቋማት አካባቢ የሚታየውን አካባቢያዊና ማኅበረሰብዊ ተፅዕኖን ለመቀነስ ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ዕቅዱ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም