ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለበዓል ገበያ የምርት እጥረትም ሆነ የዋጋ ንረት እንዳይኖር ዝግጅት መደረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3/2012 (ኢዜአ)  በዘመን መለወጫ በዓል የምርት እጥረትም ሆነ የዋጋ ንረት እንዳይኖር በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ካጋጠሙም ቁጥጥር ተደርጎ ሕጋዊ አርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ ዩሱፍ በሰጡት መግለጫ፤ በዘመን መለወጫ በዓል የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ወደ መዲናዋ በቂ ምርት እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።

ለበዓሉ የሽንኩርት፣ የጤፍ፣ እንስሳትና የእንስሳት ውጤቶች ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ "በበቂ ሁኔታ" መግባቱንም ተናግረዋል።

በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ17 እሰከ 20 ብር እየተሸጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ ጤፍ ወደ ከተማዋ መግባቱን ጠቅሰው በተመጣጣኝ ወጋ እየተሸጠ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሸማቹ ማኅበረሰብ ይህንን በመረዳት የሚገዛቸውን ነገሮች ተረጋግቶ መሆን አለበት ብለዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ካጋጠሙም በቢሮው በኩል ቁጥጥር የሚደረግ በመሆኑ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ኃላፊው ገልጸዋል።

የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ሌሎች ከግብይት ጋር የተያያዙ ጥቁማዎችን ለቢሮው ለማድረስ በ8588 ነፃ የስልክ መስመር መጠቀም ይቻላል ተብሏል።

ቢሮው በተለይ የቁም ከብት ግብይት በሚካሄድባቸው የገበያ ሥፍራዎች የኬሚካል ርጭት ማድረጉን ያስታወሱት አቶ አብዱልፈታ ማኅበረሰቡ ከኮሮናቫይረስ ራሱን እየጠበቀ የበዓል ግብይቱን እንዲያከናውን አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም