በላስታ ተራሮች ላይ የሚተገበረው 'ዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት" ለቱሪዝም ዕድገት የጎላ ሚና ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በላስታ ተራሮች ላይ የሚተገበረው 'ዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት" ለቱሪዝም ዕድገት የጎላ ሚና ይኖረዋል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3/2012 (ኢዜአ) ለተራቆቱት የላስታ ተራሮች አረንጓዴ ለማልበስ የተወጠነው 'ዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት' ለአገር ውስጥ ቱሪዝም ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በአማራ ክልል ትብብር የተራቆቱ የላልይበላ ዙሪያ ገባ ተራሮችን ወደ አረንጓዴ ሸማ ለመለወጥ ያለመ ፕሮጀክት ከፍተኛ መንግስታዊ የስራ ሃላፊዎች ባሉበት በትናትናው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
የመጀመሪያ ሃሳብ እንደሆነ የተገለፀለት 'ዓለመ ዕፅዋት የማደጎ ዛፍ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት' የሰው ልጅ ቀደምት መኖሪያነቱ ለተራቆተውና ለግብርና ስራ ምቹ ላልሆነው አካባቢ ተስፋ ተጥሎበታል።
የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት ማንኛውም ዛፍ በማደጎ መንከባከብ የሚሻ ሰው በአካልም ሆነ ዘመን ባፈራው የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አንዲት ዛፍ ማሳደግ የሚችልበት፣ ለዚህም ዓመታዊ ወጭ ይከፍላል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው 'የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት' ዓላማ ታሪካዊውን የላልይበላ አካባቢ ለመኖሪያ ምቹ፣ የአገር በቀል ዕጽዋት መነኻሪያ፣ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም ፍሰትና የአትክልትና ፍራፍሬ ማዕከል ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በቱሪዝም ላይ ብቻ ለተንጠለጠለው ለአካባቢው ህዝብ የስራ ዕድል ለመፍጠርና ለማደጎ ዛፍ ተሳታፊዎችም የዘመን አሻራቸውን የሚያትሙበት ዕድል ነው ብለውታል።
የአማራ ክልል የማህበራዊ ዘርፍ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ፕሮጀክቱ ትውልዱ ከተፈጥሮ ጋር ዕርቅ የሚመሰርትበት እንደሆነ አብራርተዋል።
ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ጋር አብሮ የሚሄድ ፕሮጀክት በመሆኑ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለቱሪዝም ምቹ መዳረሻ የማደረግ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በማደጎ ዛፍ ፕሮጀክቱ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በበይነ መረብ መትከል የሚችሉበት ስርዓትም ይኖረዋል።
'አንድ ሰው አንድ ዛፍ' በመትከል እንደ ሰው በማደጎ የሚያሳድግበት ስርዓት በመሆኑ ለዕጽዋቱ አድገትና እንክብካቤ በዓመት 3 ሺህ ብር መክፈል ይጠበቅበታል።
ፕሮጀክቱ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የግልና መንግስተያዊ ተቋማት በማደጎ ዛፍ በመትከል የፕሮጀክቱ አካል መሆን ይችላሉ።
የላስታ ላል-ይበላ ተራሮችን አረንጓዴ (እፅዋት) ለማልበስ ይፋ የተደረገው "ዓለመ ዕጽዋት ማደጎ ዛፍ" ፕሮጀክት ወደፊትም በዓለም ቅርስነት በተመዘገቡ ታሪካዊ ስፍራዎችና በአዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ እንደየአየር ንብረት ሁኔታው ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
የአገር በቀል እሳቤ ውጤት እንደሆነ የተገረለት ፕሮጀክት የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚያካትት በመሆኑ፣ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም እድገትም የጎላ ሚና አንደሚኖረው ሃላፊዎቹ ገልጸዋል።
በመሆኑም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች ለፕሮጀክቱ አሻራቸውን በማሳረፍ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በትናትናው የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ስነ ሰርዓት 7 ሚሊዮን ገዳማ ገቢ መሰበሰቡ ተጠቁሟል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ በመገኘት ተቋማቸውን በመወከል የማደጎ ዛፍ ተክለዋል።
ሚኒስትሯ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተቋማቸው በሰው ልጆች ላይ ከሚተገብረው ልጅን በማደጎ የማሳደግ እሳቤ ተመሳሳይነት ያለው የሰው ልጅ ለሕልውናው መሰረት የሆነውን "ዕጽዋት በማደጎ" የሚያሳድግበት ፕሮጀክት በመሆኑ አድንቀዋል።
በላልይበላ የተለያዩ አካባቢዎችን በማየታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ በዚህ ታሪካዊ ቅርስ ዙሪያ ያለውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ ለሚደረግ ስራ ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።