ፓርኮቹ ለአገር ገጽታ ግንባታ ግብዓት ሆነዋል- አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ፓርኮቹ ለአገር ገጽታ ግንባታ ግብዓት ሆነዋል- አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የተነቡት ፓርኮች የኢትዮጵያን ገጽታ ለውጭው ዓለም ለማስተዋወቅና ቱሪስቶችን ለመሳብ ግብዓት እንደሆኗቸው አምባሳደሮች ገለጹ።
ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች የወከሉ አምባሳደሮችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች የእንጦጦንና ሸገር ፓርኮችን ዛሬ ጎብኝተዋል።
ፓርኮቹ የኢትዮጵያን ገፅታ በተለየ ሁኔታ ቀይረው እንዳገኟቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
ፓርኮቹ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ባህል፣ ታሪክ፣ ራዕይና አንድነት በውስጣቸው በመያዛቸው የውጭ ጎብኚዎች በአካል መጥተው እንዲያዩ ለማስተዋወቅ ያግዘናል ብለዋል።
ፓርኮቹ ኢትዮጵያን መጎብኘት ለሚፈልጉ ሰዎች ለማስተዋወቅ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በተፈጥሮ ዕፅዋት የሚታወቀው እንጦጦ በፈጠራና ጥበብ ድንቅ ሥራ የቱሪስት መስህብ ሆኖ በማየታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ባደጉ አገሮች የሚገኙ የለሙ የቱሪስት መስህቦች በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ዕውን መሆናቸው ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደሚቻል አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል።
ፓርኮቹን መጎብኘታቸው ወደተወከሉበት ካናዳ ሲመለሱ ለሚሰሩት የአገር ገፅታ ግንባታ እንደሚያግዛቸውም አምባሳደር ናሲሴ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤትነት ገላጭ በሆነ መንገድ ፓርኮቹ መሠራታቸው ቱሪስቶች በኩራት እንዲጎበኟቸው ለመጋበዝ ያስችላል ብለዋል።
የካናዳ ቱሪስቶችን ኢትዮጵያን ለማስጎብኘት በርትተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ''በገበታ ለሀገር'' የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ አምባሳደር ናሲሴ አስታውቀዋል።
ፓርኮቹ የተፈጥሮ ይዘታቸውን ሳይቀይሩ መልማታቸው ለጎብኚዎች ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው የገለጹት ደግሞ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ናቸው።
ኢትዮጵያ የበለጸገ መስህቦች ያላት አገር መሆኗን ለውጭ ዓለም በማስረዳት ጎብኚዎች ምርጫቸው እንዲያደርጓት እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።
ከቻይና በዓመት 200 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለጉብኝት ወደተለያዩ አገሮች እንደሚጓዙ ያወሱት አምባሳደር ተሾመ፣ ኢትዮጵያ ቱሪስቶቹን ለመሳብ የሚያስችላት ጥናት በኤምባሲው መካሄዱን አስታውቀዋል።
ጥናቱን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደሚተዋወቅ ገልጸዋል።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተገደበው እንቅስቃሴ ወደ መደበኛ እስኪመለስ ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪስት መስህቦች ማስተዋወቃቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ "ባለን ሀብት ጥልቀት ማሰብ ብንችል ድንቅ ሥራዎችን በየአካባቢያችን ልንሰራ እንደምንችል ማሣያ ነው"በማለት በጉብኝታቸው የተመለከቱትን ገልጸዋል።
ከኮሮና ቫይረስ በኋላ ዳያስፖራውን ጨምሮ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ፍላጎት እያሳየ በመሆኑ ፓርኮችን መጎብኘታቸው ለአገር ገፅታ ግንባታ እንደሚያግዛቸው አክለዋል።
በኮይሻ፣ ወንጪና ጎርጎራ "ገበታ ለሀገር" በሚል ለተጀመረው እንቅስቃሴ ዋሽንግተን የሚገኙ ዲፕሎማቶች የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንደሰጡ አውስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች የወከሉ ዲፕሎማቶች ፓርኮችን መጎብኘታቸው ለሥራቸው ስንቅ እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ወከሉት አገር ሲመለሱ የአገርን ገፅታ በማስተዋወቅና ቱሪስቶችን በመሳብ ያለውን ጠቀሜታ እንደሚያስተዋውቁ አስታውቀዋል።
አምባሳደሮቹና ዲፕሎማቶች ላለፉት 15 ቀናት በሥልጠናና በሪፖርት ሲወያዩበት የነበሩ ሀሳቦችን በተግባር ለማሳየት ጉብኝቱ ጠቀሜታ እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል።