ሀዋሳ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል ዝግጅት አድርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል ዝግጅት አድርጋለች
ሃዋሳ ሃምሌ 6/2010 ሀዋሳ ከተማ እንደሚደርሱ የሚጠበቁት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ህዝቦች ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ህብረተሰቡ የፍቅርና የአክብሮት እሴቱን በሚገልጽ መልኩ ለፕሬዝደንቱ አቀባበል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ነገ ሃዋሳ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቁት የኤርትራው ፕሬዝዳንት የክልሉ አመራሮች ፣የሃገር ሽማግሌዎች፣የኃይማኖት አባቶችና የተለያዩ ህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት በሃዋሳ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ ከቢሻን ጉራቻ ከተማ እስከ ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም በፈረስ ጉግስና በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች የታጀበ የጎዳና ላይ አቀባበል እንደሚጠብቃቸውና ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ሰለሞን እንዳሉት ፕሬዝዳንቱ የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን እንደሚጎበኙና ሌሎችም መስተንግዶዎች ይኖራሉ፤ህብረተሰቡ ስለመስተንግዶው በየክፍለ ከተማው በመወያየት እንግዶቹን ለመቀበል በከፍተኛ ደስታ ዝግጅት አድርጓል፡፡ የሃዋሳ አደባባዮችና የመንገድ ዳርቻዎች የተለያየ መልእክት በያዙ መፈክሮችና የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ፎቶግራፎች ማሸብረቃቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግባለች፡፡