ቀጥታ፡

ሆራ ትሬዲንግ ለኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል፣ ለመቄዶንያና ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጷጉሜን 3/2012 (ኢዜአ) ሆራ ትሬዲንግ የድርጅቱን 15ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል፣ ለመቄዶንያና ለሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የአንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለመቄዶንያና ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ለእያንዳንዳቸው የ750 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የተገኙት የድርጅቱ ምክትል ሥራአስኪያጅ አቶ ጀማል ኢብራሂም ሆራ ትሬዲንግ ከዋናው ሥራው በተጨማሪ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ስኬታማ በሆነ መንገድ መቀጠል የሚችለው ማኅበረሰቡን ሲደገፍ መሆኑን አቶ ጀማል ጠቁመው፣ በ2012 በጀት ዓመት ብቻ  ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት 22 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ገልጸዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል አምባሳደር ወይዘሮ መሠረት መብራቴና የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሙዳይ ምትኩ ድርጅቱ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ላደረገው ድጋፍ ምሥጋና በማቅረብ በቀጣይም ድጋፉ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል።

በተለያየ የንግድ ሥራ የተሰማራው ሆራ ትሬዲንግ በነገው ዕለትም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች የግብዓት አቅርቦት መርሀ ግብር እንዲውል የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም