ቀጥታ፡

የኮሮና ወረርሺኝን ለመከላከል አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3/2012(ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጠ።

ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ወረርሺኙን ለመከላከል ፊት ለፊት ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችና ለአርቲስት ሰለሞን ተሼ (ጋጋ) እውቅና ተችሯቸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰም እነዚህ አካላት ወረርሺኙን ለመከላከል ለሰሩት ሥራ የጤና አምባሳደርነት የእውቅና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋቸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝን ለመከላከል ለሰሩት ሥራ እውቅና የተሰጣቸው ሁሉም አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የጤና አምባሳደርነት ማዕረግ የተሰጣቸው አካላት በግንባር ቀደምትነት ወረርሺኙን ለመከላከል በርካታ መስዋእትነት የከፈሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በስሩ ያሉትን የኃይማኖት ተቋማት በማስተባበር ወረርሺን ለመከላከል የተለያዩ አበረታች ሥራዎችን ሰርተዋልም ነው ያሉት።

ጉባኤው የሃይማኖት ተቋማት እንዲዘጉና አማኙ በቤቱ ሆኖ መንፈሳዊ አምልኮውን እንዲፈጽም በማድረግ ወረርሺኙ እንዳይስፋፋ እገዛ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የጤና ባለሙያዎችም ወረርሺኙን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ህይወታቸውንም ጭምር መስዋዕት አድርገው ትልቅ የጀግንነት ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አርቲስት ሰለሞን ተሼ (ጋጋ) በራሱ ተነሳሽነት በአዲስ አበባና ወደ ክልሎችም ጭምር በመሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራቱን አንስተው አወድሰውታል።

እነዚህ አካላት ወረርሺኙ እስኪያበቃ የሚሰሩትን አኩሪ ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ቀሲስ ተጋይ ታደለ፣ የህክምና ባለሙያዎችን ተወካይ ዶክተር ዳዊት ከበደና አርቲስት ሰለሞን (ጋጋ) ለተሰጣቸው እወቅና አመስግነዋል።

በቀጣይም የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝ እስኪያበቃ ድረስ የሚጠበቅብቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

በዛሬው እለት እውቅና ከተሰጣቸው አካላት ጎን ለጎን በርካታ ግለሰቦችና ተቋማትም በሃላፊነት ወረርሺኙን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም