ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት 200 ሚሊዮን ብር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍይሰበሰባል...አቶ ርስቱ ይርዳው

ሐዋሳ፣ ዻጉሜ 3/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በመጪው አዲስ ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 200 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

በዘመን መለወጫ  በዓል ምክንያት  በምርቶች ላይ አለአግባብ የገበያ ዋጋ ጭማሪ ማደረግ ተቀባይነት እንደሌለውም ገልጸዋል።

አቶ ርስቱ እንዳሉት የክልሉ ህዝብና መንግሥት ለታላቁ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ  የሚያደርጉትን ድጋፍ በአዲሱ ዓመት አጠናክረው ይቀጥላሉ።

የለውጡ አመራር ከታደገውና ኢትዮጵያዊያን እንድንኮራበት ካደረጉን ተግባራት መካከል የግድቡ  የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ተጠቃሽ  ነው ብለዋል።

በተለይ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል በውስጥና ውጭ ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ሴራዎችን በመሻገር የግድብ ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱ በእጅጉ ያስደስታል ሲሉም  ገልጸዋል።

በህዝብ ከፍተኛ ተሳትፎ እየተገነባ ላለው ግዙፍ ፕሮጀክት የክልሉ ህዝብ እስካሁን ከ1 ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ ማድረጉን ያወሱት አቶ ርስቱ ወደ አካባቢው በመጓዝም ማበረታታቱን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ሂደት ላይ የሚገኘው ይህ ሀገራዊ ፕሮጀክት  እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚደረገው ድጋፍ ለማጠናከር  በአዲሱ ዓመት 200 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ አስታወቀዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአሁኑ ትውልድ የራሱን ታሪክ እንዲስራ ዕድል የሰጠው መሆኑን ገልጸው ይህም ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ኩራት መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህ ሌላ  በዘመን መለወጫን በዓል ምክንያት በምርቶች ላይ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተቀባይነት እንደሌለው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ለማርገብ በመንግስት የሚቀርቡ የፍጆታ ዕቃዎች በየአካባቢው የማዳረስ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በየደረጃው የሚገኙ ኀብረት ሥራ ማህበራትም በምርት አቅርቦት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።

በተቻለ አቅም ወገን ለወገን መተሳሰብ ይኖርብናል ያሉት አቶ ርስቱ በተለይ ምንም ዓይነት  ምክንያት ሳይኖረ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ መንግስት በመቆጣጠር እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።

በዓሉን ሽፋን በማድረግ በህገወጥ መንገድ ለመክበር የሚደረጉ ሙከራዎችን ህብረተሰቡ ሊታገል እንደሚገባም አሳስበዋል።  

ፍትሃዊ የሆነ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር የንግዱ ማህበረሰብ ህገወጥ ተግባራትን በመከላከል የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም