ጎርጎራ በፕላን የተመራች ዘመናዊ የሃይቅ ዳርቻ ከተማ ለማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ጎርጎራ በፕላን የተመራች ዘመናዊ የሃይቅ ዳርቻ ከተማ ለማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገለጸ
ጎንደር፣ ጳጉሜ 03/2012 (ኢዜአ) በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተመረጠችው ጎርጎራ በፕላን የምትመራ ዘመናዊ የሃይቅ ዳርቻ ከተማ ለማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡
ጎርጎራ ከተማን የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም በጎንደር ዩንቨርሲቲ አዘጋጅነት ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ እንዳሉት የጎርጎራን የተፋጠነ እድገት ለማስመዝገብ በዘመናዊ ፕላን የምትመራ ከተማ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከተማዋን በአግባቡ ማልማት ከተቻለ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዘመናዊ የባህር ዳርቻ መዝናኛ ስፍራዎችና ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች ቀዳሚ የመሆን እድሉዋ ሰፊ ነው ብለዋል፡፡
የከተማዋን የወደፊት እድገት ታሳቢ በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ ምሁራን ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ከተማዋን የዘመናዊ ማስተር ፕላን ባለቤት ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
"ጎርጎራ የእምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም ለበርካታ ዓመታት በልማት ተረስታና ተዳክማ የቆየች ከተማ ናት" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸው የጎርጎራን ትንሳኤ ያበሰረ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የጎንደርንና አካባቢውን የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማነቃቃት ለበርካታ የዩንቨርሲቲ ምሩቃን ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር በኩል የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለፕሮጀክቱ መሳካት በእውቀት፣ ክህሎትና ገንዘብ ጭምር በመደገፍ ልማቱ በአጭር ጊዜ እውን እንዲሆን የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ጎርጎራ በግብር፣ ሆቴል፣ መዝናኛ ሌሎች የቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ተመራጭ አካባቢ በመሆኗ ባለሃብቶች በልማት እንዲሳተፉ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ አይቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለከተማዋ እድገት መፋጠን የበኩሉን ሀገራዊ ሃላፊነት ለመወጣት የጀመራቸው ጥረቶች ለሌሎችም መሰል ተቋማት በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በፎረሙ የጎርጎራን አማራጭ የወደፊት የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የግብርና ምቹ የተፈጥሮ ጸጋዎችን የሚያመላክቱ ሶሰት ጥናታዊ ጽሁፎች በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ለአንድ ቀን በተካሄደው ፎረም የፌደራል፣ የክልል እና ዞን የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን መሳተፋቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡