ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ለበዓሉ ከዋዜማ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ለበዓሉ ከዋዜማ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3/2012(ኢዜአ) ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ ጀምሮ በዕለቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመጠቀም ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።
በማስተላለፊያ መስመሮችና በትራንስፎርመሮች ላይ ብልሽቶች ሲያጋጥሙ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጋራ ዝግጅቶት ማጠናቀቃቸውም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በ2013 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚኖረውን የኃይል ፍልጎት ለማሟላት የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ ሊከሰት የሚችለውን የኃይል መዋዠቅንና መቆራረጥ ለመቀነስ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ በአጽንኦት ጠይቋል።
በዚህም የድንጋይና እህል ወፍጮዎች፣ የፕላስቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የኬሚካልና ሌሎች ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ አሳስቧል።
ኢንዱስትሪዎች በተለይ ከጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡00 ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 4፡00 ድረስ ከግሪድ የሚያገኙትን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉም ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።
የተቋሙ መግለጫ እንዳመለከተው በበዓል ዋዜማና በዕለቱ ቀን የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቆራረጥና ሳይዋዥቅ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ እንዲሁም ችግሩ ከተከሰተም በተገቢው መንገድ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው።
በአሁኑ ወቅትም የኃይል መቆራረጥ በተደጋጋሚ የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት በመካከለኛና በዝቅተኛ መስመሮች ላይ የኃይል ጭነትን የማመጣጠንና የቅድመ መከላከል ጥገና ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አመልክቷል።
ደንበኞች በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸው የኤሌክትሪክ ቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝቧል።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛባቸው ሰዓታት ማለትም ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባሉት ጊዚያት ቢጠቀሙ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማግኘት ባለፈ የኤሌክትሪክ መቆራረጥንም ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አገልግሎቱ አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ሥራ ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ የያዙ የቴክኒክ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለሥራ ጉዳይ ስለሚንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ተቋሙ አስገንዝቧል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተቋሙ የጥገና ሠራተኞችን በመምሰል መሠረተ ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ጨምሮ የገለጸው።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችን በመጠበቅ እንዲተባበርና ያልተገቡ ተግባራት ሲፈጸሙ ከተመለከተ ለሚመለከታቸው የሕግ አካላት እንዲያሳውቅ አስገንዝበዋል።
ደንበኞች ማንኛውንም መረጃዎች ለመጠየቅ፣ ጥቆማዎችና አስተያይቶች ለማቅረብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሔድ ወይም በ905 ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከል ማሳወቅ እንደሚችሉ አገልግሎቱ ጠቁሟል።