የአዕምሮ ህሙማንን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መጠበቅ ይገባል - የጤና ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአዕምሮ ህሙማንን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መጠበቅ ይገባል - የጤና ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3/2012(ኢዜአ) ህብረተሰቡ የአዕምሮ ህሙማንን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መጠበቅ እንዳለበት የጤና ባለሙያዎች አሳሰቡ፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መነሻውን ከቻይናዋ ሁዋን ከተማ በማድረግ በዓለም ላይ 27 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፤ ከ900ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡
ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወዲህከ59 ሺህ በላይ ዜጎች በበሽታው በመያዝ በአገር ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን አሳድሯል፡፡
የወረርሽኙን ተጋላጭነት ስንመለከት ደግሞ በተለይ የአዕምሮ ህሙማን ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከሌሎች ዜጎች አንጻር ሲታይ የከፋ ያደርገዋል፡፡
ሕሙማኑ በወረርሽኙ የመጠቃት እድላቸውን እንዲሁም፣ ማህበረሰቡ ማድረግ ስላለበት ጥንቃቄ አስመልክቶ በሁሉም ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር እንዲያስችል ኢዜአ በመስኩ የተሰማሩትን ባለሙያዎች አነጋግሯል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 የአዕምሮ ጤና ሥነ-ልቡና ባለሙያና የማህበራዊ ድጋፍ ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ ኖህ ውብሸት እንደገለጹት፣ የአዕምሮ ህሙማንን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ የቤተሰብ፣ የማህበረሰብና የማቆያ ማዕከላት ድርሻና ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
እነዚሁ ሕሙማኑን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ንጽህናቸውን የመጠበቅ፣ የሚኖሩበትን ሥፍራ የማጽዳትና ከሌሎች አካላት ጋር የሚኖራቸውን ንክኪ ለመቀነስ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዮናስ ላዕቀ በበኩላቸው፣ ለህሙማኑ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ለሕክምና ባለሙያዎችም የስነ-ልቡና ድጋፍ ቢደረግ የህሙማኑን ተጋላጭነት ለመቀነስ ያግዛል ባይ ናቸው፡፡
በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት አቶ አንተነህ መሃሪ እንደሚሉት ደግሞ "ሁሉም አካል ራሱን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ጥንቃቄ እንደሚያደርገው ሁሉ፤ ለአዕምሮ ሕሙማንም በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ጥንቃቄ ሊያደርግላቸው ይገባል"።
ሕሙማኑን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ዜጎች አድሎና መገለልን ሳይፈጥሩ መርዳትና መደገፍ እንዳለበት የመከሩት ደግሞ በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ክፍል አስተባባሪ አቶ ታምሩ ያለው ናቸው፡፡
ህብረተሠቡም የተጠቀመባቸውን ማስኮች፣ ማስቲካ፣ የጫት ቁርጥራጮች፣ የታሸገ ውሃና የመጸዳጃ ወረቀት(ሶፍት) በተገቢው መንገድ በማስወገድ የሕሙማኑን ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚኖርባቸው ሙያተኞቹ መክረዋል፡፡
ህብረተሠቡ የአዕምሮ ህሙማንን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይጠቁ ከማገዝ በተጨማሪ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን በማከናወን ሰብዓዊ ግዴታን መወጣት እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል፡፡