የካፍ አዲሱ የአሠልጣኞች የሥልጠና አሰጣጥ የመግባቢያ ሰነድ ተግባር ላይ ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
የካፍ አዲሱ የአሠልጣኞች የሥልጠና አሰጣጥ የመግባቢያ ሰነድ ተግባር ላይ ዋለ
አዲስ አበባ ጷጉሜን 3/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አዲሱ የአሠልጣኞች የሥልጠና አሰጣጥ የመግባቢያ ሰነድ ተግባር ላይ መዋሉን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን "የካፍ የመግባቢያ ሰነድ የወጣበት ምክንያት የእግር ኳስ ሥልጠናና የጥራት ጉዳይን ለማስተካከል በማለም መሆኑን" ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ይህንን የመግባቢያ ሰነድ ሥምምነት ፈርሞ መላኩንም ገልጸዋል።
በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ወጥ የሥልጠና ማንዋል የሚዘጋጅ ሲሆን አባል ሀገራቱ ማንዋሉን መሠረት በማድረግ የራሳቸውን የሥልጠና ማንዋል እንዲያዘጋጁ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
የካፍ ከፍተኛ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እንደገለጹት የመግባቢያ ሰነዱ ሞሮኮ ላይ በነበረዉ ስብሰባ መዘጋጀቱንና ኢትዮጵያ በሂደቱ ላይ ከተሳተፉት ሀገሮች አንዷ ናት።
አህጉሪቷ በምትጠቀምበት የኢንስትራክተሮች መመሪያ ላይ አባል ሀገራቱ ከተነጋገሩበት በኋላ በቋንቋና በዞን ተከፋፍሎ የመግባቢያ ሰነዱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ ለአባል ሀገራቱ በአራት ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዐረብኛና በፖርቹጊስ ቋንቋ ተዘጋጅቶ መላኩን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በሴካፋ ዞን በሚገኙ 14 የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሀገሮች መካከል በመካተት ሥልጠና ትወስዳለችም ብለዋል።
በአዲሱ የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ከዚህ በፊት በሦስት ደረጃ ብቻ ይሰጥ የነበረው ሥልጠና ማደጉንም ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ከሲ፣ ከቢና፣ ከኤ ላይሰንስ በተጨማሪ ከላይ የፕሮ እና ከታች የዲ ላይሰንስ ሥልጠና መጨመሩንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የአካል ብቃትና የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ ለመሆንም የቢ ላይሰንስ መያዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የፉትሳል አሠልጣኝ ለመሆንም የሲ ላይሰንስ ቀድሞ መያዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከ15 እስከ 40 ሰዓት የሚወስዱ የማነቃቂያ ኮርሶችንም አባል ሀገራቱ እንዲሰጡ መወሰኑን ኢንስትራክተር አብርሃም አስረድተዋል።
የካፍ የመግባቢያ ሰነድ ስምንት መመዘኛ ነጥቦች የተካተቱበት ሲሆን በወረቀት አስፍሮ ለአባል ሀገራቱ መላኩ የሚታወስ ነው።