ቀጥታ፡

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ700 ሺህ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን እያሰራጨ ነው

ድሬዳዋ ጳጉሜ 2 / 2012 ኢዜአ -የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ለ700 ሺህ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን እያሰራጨ መሆኑን አስታወቀ። 

የዩኒቨርሲቲው የተመራማሪዎችና የአርሶ አደሮች የምርምር ቡድን አባላት በባቢሌ ወረዳ እየተካሄደ ያለውን የስኳር ድንች ልማት ትላንት በመስክ ጎብኝተዋል ።

በዩኒቨርሲቲው የምርምር የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ተመራማሪ ዶክተር ደንደና ገልሜሳ ዩኒቨርሲቲው ከታህሳስ 2011 ዓም ጀምሮ  በአስራ አንድ የስኳር ድንች ዓይነቶች ላይ የምግብ ንጥረ ነገር ይዘት ልየታና የዝርያ ማሻሻል ምርምር እያካሄደ ነው ።

ምርምር እየተካሄደባቸው ካሉ የስኳር የድንች አይነቶች ውስጥ የሶስቱ ስራቸው ተጠናቆ ዝርያቸውን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መጀመሩን ተናግረዋል ።

ለአርሶ አደሩ እየተሰራጩ ያሉት የስኳር ድንች ዝርያዎች ዲላ፣ አልሙራና ከቡዲ የተሰኘ ስያሜ የተሰጣቸውና በምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸው የበለጸጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

 በምስራቅና በምዕራብ ሐረርጌ  ለ700 ሺህ አርሶአደሮች ዝርያዎቹን ማሰራጨት መጀመሩን አመልክተዋል ።

የስኳር ድንች ዝርያዎቹ በሶስት ወር ጊዜ ለምርት የሚደርሱና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

"በቫይታሚን "ኤ"፣ አይረንና፣ ዚንክ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ በመሆናቸውም በእርግዘና ወቅት በእናቶች ሰውነት የደም እጥረት እንዳያጋጥም የሚረዱና የህጻናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የሚረዱም ናቸው" ብለዋል።

የምርምር ፕሮጀክቱ በአንግሊዝ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚካሄድና ለቀጣይ ለሶስት ዓመት የሚዘልቅ መሆኑን አመልክተዋል ።

ፕሮጀክቱ  በደቡብ 600 ሺህ አርሶአደሮችን ጨምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር፣ የሐረሪና የሶማሌ ክልሎችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ዶክተር ደንደና አስታውቀዋል ።

የባቢሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊም በከር ዩኒቨርሲቲው የገጠሩን ህብረተሰብ ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል እያደረገ ያለው ድጋፍ አርአያ መሆኑን ገልጸዋው።

"በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ባለፉት ሶስት ወራት በ430 ቤተሰቦች ማሳ ላይ የተተከሉ የስኳር ድንች ዝርያዎች የተጀመረውን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ተግባር ለማሳካት አስተዋጻ አላቸው"ብለዋል።

በመስክ ጉብኝቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮችም ዩኒቨርሲቲው የግብርና ስራቸውን ለማሻሻል እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ  አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም