ቀጥታ፡

ፕራይቬታይዜሽንን የምንተገብረው ለሀገር ባለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ነው... ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2/2012 (ኢዜአ) "ፕራይቬታይዜሽንን የምንተገብረው በየትኛውም አካል ተገደን ሳይሆን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች የኦፕሬተርነት ፍቃድ ወስደው እንዲሰሩ መንግስት ውሳኔ ማሳለፉም ተገልጿል።

ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ የሚገቡ የቴሌኮም ኩባንያዎችንና የኢትዮጵያ ቴሌኮም ድርሻ ማሻሻያዎችን  በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት የባለድርሻ አካላት ወይይት ተደርጓል፡፡

ውይይቱ በፍቃድ አሰጣጡና ማሻሻያ ሂደቱ ላይ ግብዓት ማሰባሰብን ያለመ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ የግል ድርጅቶችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፈውበታል።

በመድረኩ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ኢትዮጵያ ላላፉት በርካታ ዓመታት የተከተለችው የፋይናንስ ፖሊሲ በማክሮ ኢኮኖሚዋ ላይ መዛባት ማምጣቱን አብራርተዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ችግሩን ማቃለል ያስቻሉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መተግበራቸውንም ጠቁመዋል።

ከማሻሻያዎች አንዱ የሆነውን የቴሌኮም ዘርፍ ለማሻሻል ደግሞ በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ነው የገለጹት።

የግል ዘርፉን ለማሳተፍ የሚያስችሉ ጥልቅ ጥናቶችን ከማካሄድ በተጨማሪ ራሱን ችሎ ዘርፉን የሚመራ ተቋም መቋቋሙን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በተከናወኑት ተግባራት ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ መደረጉንም አንስተዋል።፡

የማሻሻያው ዋነኛ አላማ በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ዘርፈ ብዙ እድገት ማስመዝገብ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረት ሁለት ተጨማሪ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ፍቃድ ወስደው እንዲሰሩ ወሳኔ ተላልፏል ብለዋል።

ውድድሩን ጤናማ ለማድረግ ሲባል ወደ ስራ የሚገቡ የቴሌኮም ኩባንያዎች ቁጥር ተገድቧልም ነው ያሉት።

አሸናፊ የሚሆኑት ሁለቱ ኩባንያዎች በቅርቡ በሚወጣው ጨረታ የሚለዩ ይሆናልም ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በሚመለከት በቀጣይ 40 በመቶ ድርሻ ለተመረጡት ኩባንያዎች የሚተላለፍ ሲሆን 5 በመቶ ድርሻ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን የሚሸጥ ይሆናል።

ቀሪው 55 በመቶ ድርሻ ደግሞ በኢትዮ ቴሌኮም ስር እንደሚሆንም ነው ዶክተር ኢዮብ የገለጹት።

"አጠቃላይ ሂደቱ ለህዝብ በየጊዜው ስለማይገለጽ ብዥታን ፈጥሯል፤ አሁን ላይ እንዲሸጡ መወሰናችን የውጭ ሃይሎች ግፊት ስለፈጠሩብን ነው ወይ" የሚሉ ሀሳቦች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል።

የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ከወዲሁ ለስራው ማዘጋጀት እንደሚገባም ነው አስተያያት የሰጡት።

አሁን ላይ በስራ ላይ ያሉት የኢትዮ-ቴሌኮም ሰራተኞች እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ በግልጽ ሊነገር እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮ-ቴሌኮም የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ በርካታ ሪፎርሞች መሰራታቸውን አስታውሰዋል።

ድርጅቱ አሁን ላይ በአንጻራዊነት የተሻለ ቁመና ላይ ቢገኝም የሚጠበቅበትን አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ግን ክፍተቶች መኖራቸውን ነው ያብራሩት።

ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ የግሉን ሴክተር ማሳተፍ ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም።

በመሆኑም ፕራይቬታይዜሽንን የምንተገብረው የትኛውም የውጭ ሃይል አስገድዶን ሳይሆን ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ተገንዝበን ነው ብለዋል።

"ለዚህ ደግሞ መንግስት በህዳሴ ግድብ ላይ ያለው አቋም ጥሩ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ሁለት ተጨማሪ የቴሌኮም ኩባንያዎች ወደ ገበያው መቀላቀላቸው የዘርፉ ባለሙያዎችን ስራ የሚያፈናቅሉ ሳይሆን ተጨማሪ ስራና አማራጭ የሚፈጥሩ ናቸው።

በኢትዮ-ቴሌኮም የሚሰማሩ ኩባንያዎች አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በሞባይል ባንኪንግ ዘርፍ እንደማይሰማሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ግብዓትን ለማሰባሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚካሄደው ውይይት ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም