ቀጥታ፡

ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2/2012 (ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የአገርንና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን አስታወቀ።


ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው የ2012 ዓመት ከገቢና ወጭ እቃዎች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ በመያዝ ለመንግስት ገቢ ማድረጉን አስታውቋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ማረጋጋት መቻሉንም ገልጿል።

በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጥበቃ እንዲያገኙ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና በህገ ወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ አድርጓል።

በ2013 ዓመትም በህገ መንግስቱ መሰረት የተጣለበትን ህዝባዊ ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ህዝቡ የጣለበትን ህዝባዊ ሃላፊነት በመወጣት ለኢትዮጵያ ሰላም ደህንነት ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ ተግቶ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ለዚህም የፖሊስ አባላቱ ተልዕኳቸውን በሚፈጽሙባቸው ቦታዎች ሁሉ ቀልጣፋ የወንጀል መከላከል ስራ መስራት እንዲችሉ ዘመናዊ ግብአቶች እየተሟሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመገምገምና በየአካባቢው ያሉ የወንጀል አዝማሚያዎችን ቀድሞ በማወቅና በመተንተን ለጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉትን በመለየት አስቀድሞ የመከላከልና የመፍታቱ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራልም ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ የአገርን ሰላምና ደህንት ለማስከበር በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው ላሉ የፖሊስ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ህብረተሰቡን በዓሉን ሲያከብር ራሱን ከኮቪድ-19 እና ከወንጀል ለመከላከል ከፖሊስ ጎን እንዲሰለፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም