ቀጥታ፡

የዱር እንሰሳት ለቱሪዝም ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ፓርኮችን በአግባቡ ማልማት ያስፈልጋል-ባለሰልጣኑ

አዳማ ጳጉሜ 2/2012(ኢዜአ) የዱር እንሰሳት በቱሪዝም ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው መጠለያና ፓርኮችን በአግባቡ ማልማት እንደሚያስፈልግ የዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ በዘርፉ የቀጣይ ዓመት መሪ እቅድ ዙሪያ በአዳማ ከተማ ከክልሎችና ፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት ዘርፉን በሚፈለገው መልኩ ማልማት ባለመቻሉ በሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ውስጥ እየተጫወተ ያለው ሚና  ዝቅተኛ ነው።

በዱር እንሰሳት መጠለያ ደን ላይ እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋ፣ሰደድ እሳት፣ የግጦሽ መስፋፋት፣ ህገወጥ ሰፈራና አደን እንዲሁም ያልተመጣጠነ ኢንቨስትመንት በፓርኮች አካባቢ መከናወን የዘርፉ ቁልፍ ችግሮች ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።

የዱር እንሰሳቱ በቱሪዝም ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው መጠለያዎችንና ፓርኮችን በአግባቡ ለማልማት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ ኩመራ ገልጸዋል።

በተለይም የዱር እንሰሳት መጠለያና ፓርኮች አካባቢ የመሰረተ ልማትና የቱሪስት ማረፊያዎች ችግር እንዲሁም  ሎጆችና ተጓዳኝ  መገልገያዎች በተገቢው ያለመመቻቸታቸው የዘርፉ  ማነቆዎች እንደሆኑ  አመልክተዋል።

የአስር ዓመቱ እቅድ የዱር እንሰሳቱን አማራጭ የኢንቨስትመንትና የሃብት ምንጭ ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታትና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ዘርፉን በማልማት ከሃብቱ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆንና በባለቤትነት እንዲመራው በደን ልማት፣ ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ  ላይ በብሔራዊ ፓርኮች በዘላቂነት የሚከናወን ተግባር እንደሚኖርም አስረድተዋል።


የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የስነ ምህዳር ጥበቃ ቁልፍ ሚና አለው ያሉት ደግሞ የአካባቢና አየር ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ናቸው።

"ዋናው የዱር እንሰሳት መጠለያ ደን ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብርም በደን ልማት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በተፈጥሮ ሃብት ልማት እንዲሳተፍና ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል አለብን፤ለቱሪዝምና  ብዝሃ ህይወት ልማት የዱር እንሰሳት ያላቸው ሚናም የላቀ ነው ብለዋል።

እቅዱ ሃብቱ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ብሎም  ዱር እንሰሳት ልማትና  ጥበቃ  የሚበጅ መሆኑንም አመልክተዋል።


በተለይም አደረጃጀትን ፣ህጎችና አሰራሮችን በማሻሻል ሃብቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።


በዱር እንሰሳት መጠለያና ፓርኮች አካባቢ በመሰረተ ልማት ጥገና፣ ስነ ምህዳር ጥበቃና ችግኝ ተከላ ከሰባት ሺህ በላይ  ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ እድል መፈጠሩን ከዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን  የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም