በሰላም ማረጋገጥ የተመዘገበን ስኬት በአዲሱ ዓመት በልማትና ኢንቨስትመንት ይደገማል - ኢዜአ አማርኛ
በሰላም ማረጋገጥ የተመዘገበን ስኬት በአዲሱ ዓመት በልማትና ኢንቨስትመንት ይደገማል
ባህርዳር ጳጉሜ 2/2012ኢዜአ በአማራ ክልል ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ የተመዘገበን ውጤት በአዲሱ ዓመት በልማትና ኢንቨስትመንት ለመድገም በትጋት ይሰራል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ የ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክተው ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው "ባለፈው ዓመት በክልላችን የነበረውን ያለመረጋጋት ችግር ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ የሰላም አሴቶችን ለመገንባት በቅተናል" ብለዋል።
የተፈጠሩ ችግሮችንና ፈተናዎችን ለመቅረፍ በተደረገ ጥረት በገጠርና በከተማ ረብሻ የሚፈጥሩ አካላትን በሰላማዊ መንገድና ህግና ስርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት የማስተካከል ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል ።
በክልሉ በነሐሴ 2012 ዓም በተጀመረ ዘመቻ ለ100ሺህ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ታቅዶ 132 በመቶ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከጤና ሚኒስቴር የላቀ አፈጻጸም ሽልማት ማግኘቱን አውስተዋል።
በክልሉ ሰላም በመስፈኑ ልማትና ኢንቨስትመንት ከመነቃቃቱ ባሻገር ግንባታቸው እየተፋጠኑ ከሚገኙ ሶስት ግዙፍ የዘይት ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ የሙከራ ምርት መጀመሩን ተናግረዋል ።
"በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በሚከናወነው የከተሞች መሰረተ ልማት ግንባታ ክልሉ በአገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ በመውጣት 600ሚሊዮን ብር የነበረውን ዓመታዊ የበጀት ድጋፍ በእጥፍ እንዲያድግ ማድረግ ተችሏል"ብለዋል።
በ2013 አዲስ ዓመት ለጣና ዙሪያ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሃይቁን ከእንቦጭ አረም ነጻ የማውጣት ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል ።
የጎርጎራ ፕሮጀክትን ለማሳካት ትኩረት እንደሚሰጥ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ በስፍራው ለሆቴልና ቱሪዝም ልማት የሚውል 276 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል ።
በስፍራው ከሚገነቡ መሰረተ ልማቶች መካከል አትሌት ሃይሌ ገብረ ስላሴ በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚያቋቁመው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል እንደሚገኝበት ጠቁመዋል ።
የክልሉ ልማት ማነቆ የሆነውን የሲሚንቶ እጥረት ለመቅረፍ ከአባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ በተጨማሪ ፈቃድ የተሰጣቸውን ሁለት ፋብሪካዎች እስከ ሶስት ዓመት ጊዜ ውሰጥ ለማጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል ።
"በግብርናው ዘርፍ በወረዳዎች የተጀመሩ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት አርሶ አደሩን ከኋላ ቀር የአመራረት ዘይቤ ወደ መካናይዜሽን እንዲሸጋገር ይደረጋል" ብለዋል ።
ክልሉ ልዩ ትኩረት በሚሰጣቸው በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በመዕድንና በቱሪዝም ልማት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል ።
"በባህርዳርና ሌሎች ከተሞች ሰላም በማስፈን የተመዘገበውን ውጤት በአዲሱ ዓመት አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካለት ጋር ይሰራል" ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በዓሉ የሰላም፣ የብልጽግና፣ ሁሉም ሰርቶ የሚለወጥበት የተግባር ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።