ለሰላምና ደህንነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና አሰጣጥ ስነ- ስርዓት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላምና ደህንነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና አሰጣጥ ስነ- ስርዓት እየተካሄደ ነው
ባህር ዳር ጳጉሜ 2/2012(ኢዜአ) በአማራ ክልል ለተገኘው ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በባህርዳር ከተማ የእውቅና አሰጣጥ ስነ-ስርዓት እየተካሄደ ነው።
''ለዘላቂ ልማትና አብሮነት የህግ የበላይነት እናረጋግጣለን'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው በዚሁ ስነ-ስርዓት የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች እንዲሁም የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የክልሉ የሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ገደቤ ሃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት እውቅናው እየተሰጠ ያለው በፀጥታው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበከረቱ 150 የፀጥታ፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ወጣቶችና ሌሎችም አካላት ነው።
ከእነዚህ ውስጥ 30 የሚሆኑ የፀጥታ አካላት ከረዳት ኢንስፔክተርነት እስከ ምክትል ኮሚሸርነት የማዕረግ እድገት ሽልማት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
እንዲሁም 20 የሚደርሱ የልዩ ኃይል ብርጌድ አመራሮች፣ የአድማ ብተና አመራሮችና የመከላከያ ሰራዊት አባላትም አውቅና ከሚሰጣቸው ውስጥ ይገኙበታል።
በተጨማሪም በአጎራባች ክልሎች በጥምረት በተሰራው የሰላምና ደህነንት ስራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች የፀጥታ ተቋማትም እውቅና ይሰጣል ብለዋል።
በእውቅና አሰጣጥ መድረኩ ላይም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።