በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት ተጠናቋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት ተጠናቋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 1/2012(ኢዜአ) በሳዑዲ አረቢያ ርዕሰ መዲና ጅዳ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ የጉዞ ሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁን በጅዳ የኢፌዴሪ ቆንስል አስታወቀ።
የጉዞ ሰነድ ከተዘጋጀላቸው ኢትዮጵያውያን ውስጥ 2 ሺህ የሚሆኑት በቅርቡ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጅዳ የኢፌዴሪ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር አብዱ ያሲን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጅዳ ካሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን መካከል የጉዞ ሰነድ የተዘጋጀላቸውን ወደአገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው።
በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ከሚገቡት 2 ሺህ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ሴቶች፣ ህጻናትና ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
እንደ አምባሳደር አብዱ ገለጻ፤ በህገ ወጥ መንገድ በቀይ ባህር በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ ሴቶችና ወጣት ወንዶች ናቸው።
“በሳዑዲ አረቢያ ድንበር አካባቢ ያለውን የጦርነት ቀጣና አልፈው የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ7 ሺህ እስከ 10 ሺህ ይደርሳል” ብለዋል አምባሳደር አብዱ።
ከሳዑዲ አረቢያ ድንበር ተይዘው ወደ እስር ቤት የሚወሰዱ ዜጎችን የጤንነት እና የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ቆንስል መስሪያ ቤቱ ከአገሪቱ መንግስት ጋር በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
''በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚሰራጩት መረጃዎች ከእውነት የራቀ ነው'' ያሉት አምባሳደር አብዱ፤ በጅዳ የሚገኘው ቆንስል መስሪያ ቤት ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲገቡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም በፌዴራል መንግስት በኩል አገር አቀፍ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተከሰተበት በመሆኑ በጅዳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን በአንድ ጊዜ ወደ አገር ቤት ለመመለስ አዳጋች እንዳደረገው አምባሳደር አብዱ አስረድተዋል።
በጅዳ እስር ቤትና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ መንግስት ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አምባሳደር አብዱ፤ በአገር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸው እና በእስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን በትዕግስት እንዲጠባበቁም ጠይቀዋል።