አዲሱ ዓመት የተስፋ፣ ሰላምና የፍቅር ዓመት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ማበርከት አለበት---የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ዓመት የተስፋ፣ ሰላምና የፍቅር ዓመት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ማበርከት አለበት---የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 1/2012 (ኢዜአ) አዲሱ ዓመት የጸጥታ ችግሮች ተወግደው የብሩህ ተስፋ፣ የሰላም እና የፍቅር ዓመት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ማበርከት እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች መጪው አዲስ ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወደሌላው ምዕራፍ የሚሸጋገርበት እንዲሆንም ተመኝተዋል።
በኢትዮጵያ እየተገባደደ ባለው የ2012 ዓ.ም የተከናወኑ መልካም ተግባራት የመኖራቸውን ያህል በጸጥታ ችግር ብዙ ያልተገቡ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዓመት ጭምር ነበር።
የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም በመላ አገሪቱ እየተስፋፋ በመምጣቱ አገርና ህዝብን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
ከቀናት በኋላ የምንቀበለው አዲስ ዓመት በአገራችን የተስተዋሉ ችግሮች ተወግደው ሰላም የሚሰፍንበት፣ ዜጎች በልዩነት ከመከፋፈል ይልቅ በአንድነት የሚቆሙበት፣ ፍትህ የሚነግስበት እንዲሆንም ነዋሪዎቹ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዓመቱ በየጊዜው የሚገጥሙ ፈተናዎችና ህዝብን የሚጎዱ ችግሮች ተወግደው በህዝቦች ዘንድ አዲስ ተስፋ፣ ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት እንዲጎለበት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ነዋሪዎቹ በአገሪቱ የተከሰቱ ችግሮች ወደአዲሱ ዓመት ተከትለው እንዳይመጡ ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ያለሰላም የትም መድረስ እንደማይቻል የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ መጪው አዲስ ዓመት የህዝቦች አብሮነት የሚጠናከርበትና አርስ በርስ መተሳሰብና መግባባት የሚፈጠርበት እንዲሆን ተመኝተዋል።
መጭው ዓመት ብሩህ ተስፋ ያለበትና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአንደኛው ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ምዕራፍ የሚሸጋገርበት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።