አዲሱን አመት አብሮነትን በማጠናከርና የሰላም መሳሪያ በመሆን ልንቀበለው ይገባል - የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱን አመት አብሮነትን በማጠናከርና የሰላም መሳሪያ በመሆን ልንቀበለው ይገባል - የሃይማኖት አባቶች
አደስ አበባ ፣ ጳጉሜ 1/2012 (ኢዜአ) አዲሱ አመት አብሮነትን በማጠናከርና የሰላም መሳሪያ በመሆን በተስፋና አዲስ መንፈስ መቀበል እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።
የሃይማኖት አባቶቹ በመላው አለም ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆንም ተመኝተዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ በመጪው አዲስ አመት ፈጣሪ የሚሰጠውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ይገባል።
2012 ዓ.ም የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተስተዋሉበት መሆኑን በማስታወስ መጪው አመት የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የፍቅር እንዲሆን ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ አዲሱ አመት ጨለማና ብርዱ ወጥቶ ልምላሜና ውበት የሚታይበት እንዲሆን በመመኘት፤ ዓመቱ ከክፋት የምንርቅበት እንዲሆንም ተመኝተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ የድሬዳዋና ጅቡቲ ሐገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ዘመኑ የሰላምና የስኬት እንዲሆን ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ ሼህ ቃሲም መሀመድ ታጁዲን ''መጪው አዲስ አመት የአንድነትና የመተሳሰብ እንዲሆን ፀሎታችን ነው'' ብለዋል።
''ሁሌም በሰላም እንድንኖር መፅሀፍ ይመክረናል'' ያሉት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ፅህፈት ቤት ዋና ፀሀፊ ዶክተር አባ ተሾመ ፍቅሬ፤ በአዲሱ አመት ህዝቡ የሰላም መሳሪያና ምንጭ ሆኖ በመተሳሰብ እንዲኖር ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ 2013 ዓ.ም ክፋት ተወግዶ እውነተኛ በሆነ ፍቅርና መተሳሰብ በጋራ የምንቆምበት እንዲሆን ተመኝተዋል።
በአዲስ አመት አዲስ እቅድ በመያዝ ለማሳካት የሚታተርበት መሆኑን ያነሱት የሃይማኖት አባቶቹ፤ ''የተሰጠንን የጊዜ ስጦታ በአግባቡ ከተጠቀምንበት አዲስ ይሆንልናል'' ብለዋል።
እንዲሁም አዲሱን አመት በምህረትና በተስፋ መቀበል እንደሚገባና ያልተግባቡ የሚግባቡት እንዲሆንም ተመኝተዋል።
በአዲሱ አመት ከቀያቸው የተፈናቀሉትን መልሶ ማቋቋም በአብሮነት ላይ ውይይት ማድረግና ትውልዱን ስለአብሮነት እሴቶች የምናሳውቅበት እንዲሆንም ጠይቀዋል።
የተለያየ ሃሳብ ያላቸው በሃሳብ የሚሸናነፉበት እንዲሆንም ተመኝተዋል።