ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ቅሬታ እያቀረቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ቅሬታ እያቀረቡ ነው
አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2010 በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ''በተመሳሳይ ወንጀል ሌሎች አካባቢዎች ተፈትተው እኛ አልተፈታንም'' የሚል ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡ የህግ ታራሚዎቹ የዱላ ግርፋት፣ ጥፍር መንቀልና ማኮላሸት የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው እንደሆነም ገልጸዋል። በተጨማሪም የምግብና የማደሪያ ቤት ንጽህና ጉድለት እንዳለባቸው በመግለጽ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ''የህግ ታራሚዎቹ ቤት ውስጥ አስለቃሽ ጭስ ተተኩሶብን ጉዳት ደርሶብናል'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ በበኩላቸው የህግ ታራሚዎቹ ትናንትናና ዛሬ የምግብ አድማ እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡ ታራሚዎቹ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት በተገቢ መንገድ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ የህግ ታራሚዎቹ እያቀረቡ ያለውን 'ከእስር እንለቀቅ' ጥያቄ የፌዴራል ማረሚያ ቤቱ መመለስ እንደማይችል ያመለከቱት ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ፤ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጥበት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የህግ ታራሚዎቹ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘ ያነሱትን ቅሬታ 'ትክክል አይደለም ምንም አይነት ጉዳት በታራሚዎች ላይ አልደረሰባቸውም' ብለው አስተባብለዋል፡፡ ''ከምግብ ንጽህና ጋር በተያያዘም የተነሳው ጥያቄ ከዚህ ቀደም ይቀርብ ከነበረው ምንም ልዩነት አልተደረገም'' ብለዋል፡፡ አስለቃሽ ጭስ የተተኮሰው የህግ ታራሚዎቹ በር ገንጥለው ለማምለጥ ሲሞክሩ እንደሆነ ዋና ሱፐር ኢንተንደንቱ ተናግረዋል፡፡