አዲሱን አመት ልባዊ በሆነ ይቅርታ መሻገር እንደሚገባ የሃይማኖት መሪዎች አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱን አመት ልባዊ በሆነ ይቅርታ መሻገር እንደሚገባ የሃይማኖት መሪዎች አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 1/2012 (ኢዜአ) አዲሱን አመት ልባዊ በሆነ ይቅርታ መሻገር እንደሚገባ የሃይማኖት መሪዎች አሳሰቡ
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘወዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ጳጉሜ 1 "የይቅርታ ቀን" መክፈቻ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል።
'ፀሐይ ሳትጠልቅ ቁጣችሁን አብርዱ' በሚል መጸሃፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ንግግራቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ፤ ''የይቅርታን ትልቅነት በማስገንዘብ አዲሱን አመት በእውነተኛ ይቅርታ እንሻገር'' ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
''በዓለማችን ታሪክ ውስጥ የሰዎችን ግንኙነት አስተማማኝና ሰላማዊ ጠንካራና ተስፋ ያለው እንዲሆን ከሚያደርጉት መሰረታዊ የህይወት ክንውኖች ዋናው ይቅርታ ነው'' ብለዋል።
''በአሮጌው ዘመን ባደረግነው በደል ሁሉ ፈጣሪ ይቅር እንዲለን በየእምነታችን ይቅርታን መጠየቅ ይገባል'' ብለዋል።
መጪው ዘመን የሰላም፣ የአንድነት እና የስምምነት አመት እንዲሆን የተመኙት ብጹዕነታቸው፤ በአገር ውስጥና በውጭ ላሉ ኢትዮጵያዊያን የ'እንኳን አደረሳች' መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሃጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ በበኩላቸው ''በአሮጌው ዘመን የተሰሩትን ሃጥያቶች ባለመድገም በይቅርታ ወደ አዲሱ ዘመን መሻገር ይገባል'' ብለዋል።
''ይቅርታው አንደበታዊ እና አፋዊ ሳይሆን ልባዊ ይቅርታ መሆን አለበት'' ያሉት ተቀዳሚ ሃጂ ሙፍቲ፤ በደል ፈጻሚ ወደ ጥፋቱ ዳግመኛ ላይመለስ የይቅርታን በጎነት ሊተገብረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአገር ሰላም የሚሰፍነውና ወደ እድገት መሄድ የሚቻለው በልባዊ ይቅርታ መጓዝ ሲቻል መሆኑን ገልጸው፤ ''ከውሸት ይቅርታ በመራቅ በእውነት ብቻ መመላለስ ይገባል'' ብለዋል።
ሊቃነጳጳስ ዘካቶሊካዊያን ብጹህ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በመልዕክታቸው ''ባለፈው ዘመን የበደልናቸውንና ያሳዘናቸውን ሰዎች ይቅርታ መጠየቅ ይገባል'' ብለዋል።
''በአዲሱ አመትም ንጹህ ልብስ መልበስ ብቻ ሳይሆን ንጹህ ህሊና ይዞ መሻገር ፈጣሪም ይቅር እንዲለን ያስችላልና ይቅር እንባባል'' ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ''ከሁሉ በላይ የበደልነው አምላካችንን ነውና ይቅር በለን ብለን ዘመኑን ልንሻገር ይገባል'' ብለዋል።
''በክርስትና አስተምህሮ ይቅርታ ማድረግና አብሮነት ትልቅ ስፍራ አለው'' ያሉት ፓስተር ጻዲቁ፤ ሰው ከፈጣሪው ጋር ይቅርታን ቢፈልግ በቅድሚያ እርስ በርሱ ይቅር መባባል እንዳለበት ገልጸዋል።
በጎ እንዲደረግለት የሚፈልግ ሁሉ ከአጠገቡ ላለው ወንድሙ ይቅርታን ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
ጳጉሜ 1 "የይቅርታ ቀን" በመላው ኢትዮጵያ የይቅርታ እለት ተብሎ እየታሰበ ሲሆን በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከማለዳው ጀምሮ በርካታ የበጎ ተግባራትና የይቅርታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።