የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ተመራጭ ለማድረግ መንገዶች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ይሰራል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 1/2012(ኢዜአ) የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ተመራጭ ለማድረግ መንገዶችን ምቹና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

"ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ - እንደርሳለን!" አገር አቀፍ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጀሞ እስከ ለቡ የሳይክል እና የእግር ጉዞ በማድረግም ተከብሯል።

በእግር እና በብስክሌት የሚደረግ ጉዞ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋዎችን ለመቀነስ፣ የአካባቢ አየር ብክለት ችግሮችን ለማቀነስ፣ የማህበረሰቡ ጤና እንዲጠበቅና ተመራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ጥያቄዎችን በማስተናገድ የበኩሉን የሚያበረክት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ገልጸዋል።

የሞተር አልባ ትራንስፖርት የእግር ጉዞ፣ የሳይክል ትራንስፖርት፣ በካይነት የሌላቸው የህዝብ ትራንስፖርትን መጨመር፣ የመንገድ ደህንነትን ማሻሻል፣ የአየር ብክነትን መቆጣጠር፣ የግል ተሽከርካሪዎችን ብዛት መቆጣጠርን ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ስትራቴጂው በቀጣይ አስር ዓመታት የመንገድ ደህንነት ማሻሻል፣ የሳይክል መንገዶችን በስፋት መስራት፣ የትራፊክ አደጋ መቀነሻዎችን በስፋት መስራትና ሁሉንም ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ማጠናከር ላይ ያተኮረ እንደሆነም አመልክተዋል።

የፈጣን ትራንስፖርት መንገዶችን ማስፋፋት፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን ማሻሻልና ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት መረጃዎችን ማድረስ ሌሎች ስትራቴጂ ያካተታቸው ጉዳዮች መሆናቸው ገለጸዋል።

የሳይክል ተጠቃሚዎችን ደህንነት ማረጋገጥ፣ አዳዲስ ተጠቃሚዎችን ለመሳብና የሳክል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ፣ በከተሞች የሳይክል መንገድ እንዲስፋፉ የማድረግ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሞተር አልባ ትራንስፖርት ትልቅ አስተዋህጾ እንዳለው ተናግረዋል።

ጳጉሜን 1 ቀን የሳይክል እና የእግረኞች ቀን ሆኖ በአገር ደረጃ በሁሉም ክልል ዋና ከተሞችና በሌሎች አካባቢዎች እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም