ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት የመከላከል ሥራው ተጠናክሯል...የዞኑ ጤና መምሪያ

ፍቼ፣ ጰጉሜን 1/2ዐ12 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚስትዋለውን መዘናጋት ለማስወገድ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች የሚታየው ጥንቃቄ አልባ ግንኙነት ለቫይረሱ መስፋፋት ትልቅ ሥጋት እንደሆነባቸው አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። 

የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የኮረና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ምክትል ፀሐፊ አቶ አስፋው ደፈረ እንደገለጹት በዞኑ ከተሞችና ገጠር ቀበሌዎች የሚስተዋለውን ጥንቃቄ አልባ ግንኙነትና መዘናጋትን ለማስተካከል ትምህርትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በስፋት እየተካሄደ ነው። 

በገጽ ለገጽ ግንኙነት፣ በበራሪ ጽሑፍ፣ በሬዲዮና በእግር ጉዞ የኮቪድ 19 መተላለፊያ መንገዶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች የትምህርቱ አካል እንደሆኑም ገልጸዋል። 

በተለይ ሰው በሚበዛባቸው የእምነት፣ የገበያና የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥባቸው ሥፍራዎች ኅብረተሰቡ ሳይሰለች እጁን እንዲታጠብ፣ አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅና ንክኪ እንዲቀንስ የማስተማርና የመቆጣጠር ሥራ እየተከናወነም እንደሆነ ተናግረዋል።

በትምህርትና ግንዛቤ የመፍጠር ሂደት ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከዘጠኝ መቶ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ተደራሽ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ወደ ኮረና ቫይረስ ምርመራ ጣቢያ እንዲመጣ ተጠቂዎችም ወደ ሕክምናና ማቆያ ሥፍራዎች ገብተው ክብካቤና ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉ ወደ አንድ መቶ የሚደርሱ ሰዎች ማገገማቸውንና አራት ያህሉ ደግሞ በጽኑ ሕክምና ላይ በመሆናቸው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የቀበሌ ዐ4 ነዋሪ ወይዘሮ ፋይቱ መገርሣ የኮረና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት መንግሥት ያወጣውን አዋጅና የጥንቃቄ እርምጃ በአካባቢያቸው ጥቂት በማይባሉ ሰዎች እየተተገበረ አለመሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይም ምግብ በሚበላበት፣ ቡናና መጠጥ በሚጠጣበት ሥፍራዎች ያለው አካላዊ ርቀት የመጠበቅ፣ የፊት ማስክና እጅ የመታጠብ ችግር በርካቶችን ለበሽታው ይዳርጋል የሚል ሥጋት እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል። 

የጀበና ቡና በመሸጥ የምትተዳደረው ወጣት ማርታ ኃይሉ በርካታ ደንበኞቿ በሽታውን በመርሣት ይሁን ቸል በማለት መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ እንደማያደርጉ ተናግራለች።

በዕለት ሥራዋ ላይ ለምታገኛቸውና ለአካባቢዋ ሰዎች በተቻላት አቅም ችግሩን በማስታወስ አልኮልና ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ እንደምታደርግም ገልጻለች። 

የውጫሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ባልቻ ገመዳ በገጠራማ ሥፍራዎች የቫይረሱን አስከፊነትና ወራሪነት በመዘንጋት በሐዘን፣ በሠርግና በሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ የሚታየው መጠጋጋትና መቀራረብ ለበሽታው አጋላጭ በመሆኑ እንዲታረም ሁሉም ወገን ሊሰራ ይገባል ብለዋል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘም መጪው የዘመን መለወጫ በዓልን ተንተርሶ የሚካሄደው ግንኙነትና ማኅበራዊ ትሥሥር ላይ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንደሚከላከሉ ጠቁመው ሁሉም ይሄንን እንዲያደርግ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም