ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ይቀነሳል በሚል የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ውሳኔ ተቀባይነት የለውም... አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ይቀነሳል በሚል የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ውሳኔ ተቀባይነት የለውም... አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30 /2012 ( ኢዜአ) ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ይቀነሳል በሚል የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ውሳኔ ተቀባይነት እንዳማይኖረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።
"ለእኛ የሚሰጥ የድጋፍ ገንዘብን በመቀነስ ኢትዮጵያን አንበርክኮ የማትፈልገውን ውሳኔ በዜጎቿ ላይ እንድትወስን ሊያደርግ የሚችል ምንም ኃይል አይኖርም" ብለዋል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው ድጋፍ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጊዜያዊነት መያዟን ሰሞኑን ገልጻለች።
ውሳኔው ከህዳሴው ግድብ የማደራደር ሂደት ጋር እንደሚያያዝ አሜሪካ ብትገልፅም በኢትዮጵያ በኩል ውሳኔው ትክክል አለመሆኑንና ያላትን ትክክለኛ አቋም ለአሜሪካ አምባሳደር ማስረዳታቸውን አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።
ውሳኔው ድርድሩን በማሳለጥ በኩል አዎንታዊ ተጽእኖ እንደማይኖረውና ትክክለኛ እንዳልሆነ አስረድተናልም ነው ያሉት።
በመሆኑም የሚደረጉ ድጋፎች ከኢትዮጵያ ሉአላዊነት ጋር የሚወዳደር ባለመሆኑ፣ በውሳኔው ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነትን በመቀነስና የሚደረጉ ድጋፎችን በማስቀረት የማትፈልገውን ውሳኔ በዜጎቿ ላይ እንድትወስን ሊያደርግ እንደሚችልም አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ያላት አቋም ምክንያታዊና ህጋዊ መነሻ ያለውና ሌሎችን ለመጉዳት አለመሆኑን በውይይታቸው ወቅት ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ በሚሰጥ ወይንም በሚቀር የገንዘብ ድጋፍ የሚወሰን አለመሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም ሆኖ ወደ 120 ዓመታት የተቃረበው የአሜሪካና ኢትዮጵያ ወዳጅነት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለረዥም ዓመታት የቆየውን የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ውሳኔው የሚመጥን ባለመሆኑ፣ የአሜሪካ መንግሥት መልሶ ያየዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በዓለም አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲደረግ ተስማምተው በተጀመረበት ወቅት ድጋፉ እንዲቆይ መወሰኑ ትክክል አለመሆኑን መወያየታቸውንም አስረድተዋል።
በአሜሪካ በኩል እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች መታየታቸው ግብጽን የበለጠ ኢ-ፍትሃዊ አቋሟን አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያደርጋት መሆኑንም አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።