የሽሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 564 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሽሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 564 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ
ሽሬ እንዳስላሴ ሃምሌ 6/2010 የሽሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 564 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ፡፡ በምረቃው ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማእከሎች አስተባባሪ ወይዘሮ መዓዛ ገብረ እንዳሉት ከኮሌጁ ተመርቀው የወጡት አብዛኛዎቹ ተመራቂዎች ሥራን በመፍጠር ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በግልና በማህበር ተደራጅተው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙት ከ60 በላይ ማህበራት መካከል 27ቱ ከኮሌጁ የተመረቁ ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። ''ኮሌጁ ስራ ፈጣሪና በራሱ የሚተማመን የሰው ኃይል ከማፍራት ባለፈ ገበያን ማእከል ያደሩጉ ቴክኖሎጂዎች በማፍለቅና በመቅዳት ለቴክኖሎጂ አስፋፊዎች በማሰራጨት በኩልም ሚናውን እየተወጣ ነው'' ብለዋል። የኮሌጁ ዲን መምህር ፀጋይ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው ኮሌጁ ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሸጋገሩን አመልክተዋል። የፖሊ-ቴክኒክ ደረጃ ከተሰጠው በኋላ የሙያ ብቃት ያላቸው ሰልጣኞችን በማፍራት በኢትዮጵያ የማኑፋክቹሪንግ ማእከል ተብለው ከተመረጡ 23 ኮሌጆች መካከል አንዱ ለመሆን መብቃቱን ተናግረዋል። ዛሬ ከተመረቁት ሰልጣኞች መካከል በእንጨት ሥራ በደረጃ አራት የተመረቀችው ወጣት ዮርዳኖስ ተወልደብርሃን እንዳለችው “በሰለጠንኩበት ሙያ ወደ ሥራ በመግባት ራሴን ለመቻል በቁርጠኝነት እንቀሳቀሳለሁ”ብላለች። በአወቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ በደረጃ አምስት መመረቁን የገለፀው ጉዑሽ መብራህቶም በበኩሉ ሙያውን በአግባቡ በመጠቀም ራሱን ለመቻል በትጋት እንደሚሰራ ገልጿል። የሽሬ ፖሊ -ቴክኒክ ኮሌጅ የዛሬ ተመራቂዎችን ጨምሮ ለ5 ሺህ 721 ወጣቶችን በተለያዩ ሙያዎች በዲፕሎማ ደረጃ አስመርቋል፡፡ ከ24 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የአጭር ጊዜ ተግባር ተኮር የሙያ ስልጠና መስጠቱን ዲኑ ጨምረው ገልፀዋል፡፡