የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎረቤት አገሮች ጉብኝት ኢትዮጵያ ለክፍለ አህጉሩ ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር ያላትን ቁርጠኛ አቋም ያሳየ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት አገሮች ያደረጉት  የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ ለክፍለ አህጉሩ ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር ያላትን ቁርጠኛ አቋም ያሳየ መሆኑን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመለከተ። ሚኒስቴሩ በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው እንዳስታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ ያደረጉት ጉብኝት ውጤታማና የአገራቱን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው። መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም እንዳሉት ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ከችግር ወጥታ ከአገራቱ ጋር በጋራ ጥቅም ላይ ለመስራትና ለመልማት ያላትን ጽኑ ፍላጎት ለማሳየት ረድቷታል። ከአገሮቹ ጋር በተደረጉ ውይይቶችም በወደብ አጠቃቀም፣  በዜጎች ደህንነት፣  በመሰረተ ልማት ትስስርና በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሁኔታ ላይ በመወያየት በርካታ ስምምነቶች ተደርገዋል ብለዋል። የአገራቱን የመንግሥታትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስሰሩን የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ጠቃሚ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ በላሙ ወደብ መሬት የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የገባው ቃል ተጠቃሽ ነው። ከሱዳን ጋር በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያደረጉት ውይይትና በጅቡቲ የወደብ አጠቃቀምና አማራጮች ላይ ያደረጉት ውይይትም ጠቃሚ እንደነበር ገልጸዋል። በአገራቱ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸውና ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከአገራቱ ጋር ያደረጉት ስምምነትና የተወሰዱ እርምጃዎችም የጉብኝቱ ጠቀሜታ ማሳያ ናቸው ብለዋል። ኢትዮጵያ በቅርቡ ያደረገችው ሰላማዊ የኃላፊነት ሽግግር አገሪቷ ችግርን ያለ ሌሎች ጣልቃ ገብነት መፍታት መቻሏንና  ከችግሩ በፍጥነት የመውጣት አቅም መፍጠሯን  ያሳየ መሆኑን አገራቱ መናገራቸውን አቶ መለስ ዓለም ገልጸዋል። በዚህም በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነታቸው እንዲጠናከር ፍላጎት ማሳየታቸውንና በአገሪቷ መጥተው ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ከነዚህም ውስጥ የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትርና የቻይናው ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። በሌላ በኩል ጋዜጠኞች የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትን በተመለከተ ላነሱት ጥያቄ አቶ መለስ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከኤርትራ መንግስት ጋር ያላት ችግር በውይይት እንዲፈታ አሁንም ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም