ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ይደረጋል የተባለው ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው ነው ...ፌደሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2012 በትግራይ ክልል ይደረጋል የተባለው ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ ምርጫው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

በህገ መንግስቱ መሰረት የምርጫ ህግ ማውጣት ለፌደራል መንግሥቱ፤ ምርጫውን ማስፈጸም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሚቋቋምበት ወቅት ክልሎች ሥልጣን ይኑራቸው የሚል አንቀጽ አልሰፈረም ብለዋል።

ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያም የዓለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 ወረርሽን ለመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ተሰጥቶ ምርጫው እንዲራዘም በፌደሬሽን ምክር ቤት የቀረበውን ውሳኔ ሳይቀበል መቅረቱን ተረጋግጧል።

ምክር ቤቱ ክልሉ ምርጫ የሚያደርግበትሥልጣን እንደሌለው ቢያሳውቅም፤ በሕገ መንግሥቱ ከተሰጠው ሥልጣን ውጭ የምርጫ ሕግ በማውጣትና የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም እንቅስቃሴ ማድረጉ ትክክል እንዳልሆነ ምክር ቤቱ ተመልክቷል።

ከዚህም ባለፈ ምርጫው ሕጋዊ መሰረት የሌለውና መቆም እንደሚገባው የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ፤ የራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ  መጠየቃቸው ተገልጿል።

የትግራይ ክልል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስገዳጅነት የፌደራልም ሆነ የክልል ምክር ቤትና አስፈጻሚ አካላት ምርጫ ተደርጎ ለአሸናፊው አካል እስከሚያስረክቡ ባሉበት እንዲቀጥሉ የቀረበውን ውሳኔ ውድቅ ማድረጉ ተገቢ ባለመሆኑ በቀረቡት የውሳኔ ሃሳቦች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ አስተላልፏል።

ምክር ቤቱ ለትግራይ ህዝብ ትልቅ ክብር አንዳለው ገልጾ፤ ሕገወጥ አካላት በሚፈጽሙት ድርጊት ህዝቡ መጎዳት ስለሌለበት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቀጣይነት ያለው ጥረት ይደረጋል ብሏል።

ክልሉ ከሚያደርገው ህገ ወጥ ምርጫ ጋር በተያያዘ በትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣በራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸው ቅሬታዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተቀባይነት የሌላቸውና ሊታረም እንደሚገባቸው ገልጿል።

ቋሚ ኮሚቴው የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስልጣን ጣልቃ በመግባትና ሕገ መንግሥቱን በመቃረን በሚያደርገው ምርጫ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል።

 በተጨማሪም የፌደሬሽን ምክር ቤት ከዚህ በታች የተሰረዘሩት የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎችን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

1) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው የምርጫ ዓዋጅ ቁጥር 351/2012 ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(15) እና አንቀጽ 55(2)(መ) ጋር ይቃረናል፤

2) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምርጫ ዓዋጅ ቁጥር 351/2012ን መሰረት አድርጎ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ስልጣን ይጥሳል፤

3) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት ና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው የምርጫ ዓዋጅ ቁጥር 351/2012 ያሳለፏቸው ውሳኔዎችና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት የፌደሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የመጨረሻ ውሳኔ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም