የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ለ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመለገስ ቃል ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ለ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመለገስ ቃል ገቡ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30 /2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመስጠት ቃል ገቡ።
የተቋሙ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ እንደተናገሩት ሰራተኞቹ ደሞዛቸውን ለመለገስ ቃል የገቡት በለውጡ አመራር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜና በጥራት ተጠናቀው በማየታቸው ነው ብለዋል።
በዚህም ለፕሮጀክቱ ግንባታ 102 ሚሊዮን ብር እንደሚሰባሰብ ተናግረዋል።
ተቋሙ ከገንዘብ ባለፈ ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ከተቋሙ ሰራተኞች አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ልገሳውን ለማድረግ ያነሳሳቸው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት መከናወኑና በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት የውበትና መዝናኛ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በአገሪቱ ሶስት አካባቢዎች ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ያቀረቡትን “የገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ጥሪ ተከትሎ ተቋማት ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።