ቀጥታ፡

የአመለካከትና የተግባር አንድነትን በማጠናከር ለህዝብ ተጠቃሚነት በጋራ እንሰራለን…የሃረሪ ክልል አመራሮች

ሐረር፣ ነሐሴ 29/2012(ኢዜአ) ስልጠናው የአመለካከትና የተግባር አንድነት በመፍጠር የህዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ አቅም የፈጠረ ነው ሲሉ የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለፁ።

በክልሉ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሂድ የቆየው የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ እንደተናገሩት የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠናው አመራሩ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት የብልፅግና ፓርቲ ራዕይን ለማሳካት የሚያስችል አቅም የፈጠረ ነው፡፡

በክልሉ ቀደም ሲል በአንዳንድ አመራሮች ይታዩ የነበሩ የመገፋፋት ችግሮችን በመቅረፍ የአመለካከትና የተግባር አንድነት በመፍጠር የክልሉን ህብረተሰብ ጥያቄ ከመመለስ አንፃር በቁርጠኝነት ለመስራት መግባባት ላይ የተደረሰበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

“የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በራሳቸው ተነሳሽነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ ግንባታ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመለገስና የህዝቡን ተሳትፎም ለማጎልበት ቃል የተገባበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው እንደተናገሩት ስልጠናው አመራሩ የሚያጋጥሙትን ችግሮችን ለማለፍ ራሱን ያዘጋጀበት ነው፡፡ 

"እያንዳንዱ አመራር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይገባዋል" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም አመራሩ በክልሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከማስጀመር ባለፈ በአፋጣኝ ማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ርብርብ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

"ስልጠናው የብልፅግና ፓርቲ ተልዕኮን በተሟላ ደረጃ በመገንዘብ ሀገራዊ ለውጡን በማስቀጠል ሂደት ውስጥ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅም የፈጠረ ነው" ያሉት ደግሞ በክልሉ የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ኻሊድ አልዋን ናቸው፡፡

"ከዚህ አንፃርም ከፍተኛ አመራሩ ግንባር ቀደም ሆኖ ፈተናዎችን በብቃት መወጣት እና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይጠበቃል" ብለዋል።

"በዚህም በተለይ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አዲስአለም በዛብህ በበኩላቸው"እኛ ከፍተኛ አመራሮች የተናገርነውን በተግባር የሚንፈፅም መሆን ይጠበቅብናል”ብለዋል።

"በተለይም የህዝብን አንድነት በማጠናከር እና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በማጎልበት የሀገራችንን ብልፅግና እውን ማድረግ ይገባል" ብለዋል። 

አቶ ዘከርያ አብዱላሂ የተባሉ የክልሉ ከፍተኛ አመራር እንዳሉት በተለይም ከዚህ ቀደም የነበሩ የአመለካከት ክፍተቶችን ከማረም አንፃር ስልጠናው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

እራሳቸውን ጨምሮ አመራሩ ሃላፊነቱን በተሻለ መንገድ እንዲወጣ አቅም የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው በግላቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ 140 የሚደርሱ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም