በመጪው አዲስ ዓመት በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ይሠራል - አቶ ርስቱ ይርዳው - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው አዲስ ዓመት በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ይሠራል - አቶ ርስቱ ይርዳው
ሐዋሳ፣ ነሐሴ 29/2012 (ኢዜእ) በመጪው አዲስ ዓመት በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በትኩረት የሚሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ በቅድሚያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንኳን ለ2013 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ፤ ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅርና የአብሮነት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።
በመግለጫቸው እንዳሉት በ2012 ዓ.ም መንግሥት በክልሉ የተረጋጋ ሁኔታ በመፍጠር በሁሉም መስክ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል።
በተለይ ሕዝቦች የሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ሕጋዊ፣ ሰላማዊና በሰከነ መንገድ ማራመድ የሚችሉበትን ሁኔታ መመቻቸቱን አመልክተው መንግሥትም የሕዝብን ጥያቄ አዳምጦ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለይ የአደረጃጀት ጥያቄዎች በስፋት ነበሩ ያሉት አቶ ርስቱ ለዚህም ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል።
"50 የሚሆኑ የዞንና የወረዳ አደረጃጀት ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል፣ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ የሲዳማ ክልል ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያደረግንበት ዘመን ነው" ብለዋል።
በዚህም ከለውጡ ወዲህ እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት በተግባር የታየበት ሁኔታ እንደነበር አመላክተዋል።
በተለይ ዓመቱ የልማት ሥራዎቻችንን ማፋጠን የተቻለበት፣ በግብርና ልማትም ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ድጋፍ የተደረገበት እንደነበርም አውስተዋል።
በአረንጓዴ አሻራና የግል ባለሀብቱ ወደ ክልሉ በስፋት በመምጣት ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ በተለያዩ ልማት የተሰማሩበት ስኬታማ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
ሆኖም አሁንም ያልጨረስናቸው ሥራዎች አሉን ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ሴረኞች ጠንስስው በሚሰጡት አጀንዳዎች ኅብረተሰቡ በመደለል ወደ ግጭት የሚገባበት ሁኔታ መስተዋሉን በክፍተት አንስተዋል።
በመጪው አዲስ ዓመት በዋናነት የተጀመሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተሟላ መንገድ ምላሽ ለመስጠትና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የሚነሱ ጥያቄዎች እየመለሱ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን እንቅስቀሴ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል።
ለግሉ ሴክተር በክልሉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲኖረውና በዚህም የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ አብራርተዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶችም ከመንግሥት ጋር ያላቸው ትብብር የበለጠ የሚዳብርበት ሁኔታን ለማመቻቸት ይሰራል ብለዋል።
ከሕግና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሕዝቡ አጋልጦ በመስጠት ለሰላም ዘብ እንዲቆም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።