የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ አቀረቡ

105

አዲስ አበባ ፣ነሐሴ 29/2012 (ኢዜአ) የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ አቀረቡ።

በሲዳማ ክልል በይርጋለም ኢንዱስትሪ ፖርክ ሥራ የጀመረው "ሳንቫዶ ማኑፋክቸሪንግ ፒ.ኤል.ሲ 10ኛ ዙር የአቮካዶ ንጥረ ዘይት ምርቱን ኤክስፓርት አድርጓል።

በተመሳሳይ በቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ የጀመረው "ሪችላንድ" የመጀመሪያውን ዙር የአኩሪ አተር ዱቄት ምርት ለኤክስፓርት ማዘጋጀቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

ፋብሪካው በየቀኑ 400 ቶን የአኩሪ አተር ዱቄት ኤክስፖርት በማድረግ 200 ሺህ ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝም ነው ያመለከቱት።

ለአኩሪ አተር ፋብሪካው የሚያስፈልገው የኃይልና የጥሬ እቃ አቅርቦት ልዩ ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሪችላንድ ፒ ኤል ሲ በቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ991 ሚሊዮን 247 ሺህ ብር ወጭ የገነባው ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ሲያመርት ከኤክስፖርት ብቻ በዓመት 61 ሚሊዮን 680 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ድጋፍ 17 የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመገንባት ዕቅድ አላት፡፡

እነዚህ የግብርና ውጤት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አገሪቱ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ለመጨመር እያደረገች ያለውን ጥረት የሚደግፉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡


ፓርኮቹ ልቅ የማምረቻ ዞኖች፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማምረቻ አካባቢዎችና ግብዓቶች ተመጥነው የሚለቀቁበት ቴክኖሎጂን ያካተቱ መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት።

ከዚህ ባለፈ ዘመናዊ የግብርና ማሳዎች፣ የዕውቀትና የምርምር ማዕከሎች፣ የገጠር ማዕከሎች፣ የግብርና መሠረተ ልማቶች፣ የምርት ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች፣ የመጀመሪያ ደረጃ ማቀነባበሪያ ማዕከሎች፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት እና የግብርና ምርቶች ሽያጭ መሠረተ ልማቶች እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም