በአፋር ክልል የተስፋፋውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የተስፋፋውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው
ሰመራ፣ ነሐሴ 29/2012(ኢዜአ) በአፋር ክልል በአምስቱም ዞኖች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።
ርዕሰ-መስተዳድሩ በክልሉ አውሲ-ረሱ ዞን አደአር ወረዳ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እየተየደረገ ያለውን ጥረት በመስክ ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት እንዳሉት የአንበጣ መንጋው በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች በስፋት ታይቷል።
ክስተቱ ኑሮው በእስሳት እርባታ ላይ የተመሰረተ አርብቶ አደር ህብረተሰብ መኖ ላይና በከፊል-አርብቶ አደሩ የሰብል ልማት ላይ ጎዳት እንዳይደርስ ከፌዴራል መንግሰት ጋር በመተባበር በሄሊኮፕተርና ተሸከርካሪ በመታገዝ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም ተስፋፍቶ የተከሰተው የአንበጣ መንጋው በተወሰኑ አካላት ተሳትፎ ብቻ መከላከል እንደማይቻልና በቀጣይም በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ አጎራባች ክልሎች በመከላከሉ ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አቶ አወል አስታውቀዋል።
በክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሳትና እጽዋት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃደር መሃመድ በበኩላቸው በክልሉ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከየመንና ሱማሌ-ላንድ የተነሳ የአንበጣ መንጋ የመከለከል ስራዎች ሲከናወን መቆየቱን አውስተዋል።
ዘንደሮ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በክልሉ የወሰኑ ወረዳዎች ተከስቶ የነበረው አንበጣ መንጋ ተስፋፍቶ አሁን በ34ቱም ወረዳዎች በመድረስ በእንስሳት መኖና የለማ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ገልጸዋል።
በሄሊኮፕተር፣ ተሽከርካሪና የሰው ኃይል በመታገዝ የመከላከል ስራዎች እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዚህም 880 ሺህ ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ የቅኝት ስራዎች መካናወኑን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥም 240 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የእንስሳት መኖና ሰብል በአንበጣው መንጋ መውደሙን አመልክተዋል።
የክረምቱ ዝናብ ከአካባቢው ሞቃታማ አየር ጋር ተዳምሮ ለአንበጣው መፈልፈል ምቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው ከፌዴራል መንግሰት በተጓዳኝ የአጎራባች ክልሎች ትብብርና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአደአር ወረዳ ነዋሪ አቶ መሃመድ ኡመር በሰጡት አስተያየት አንበጣውን ለመቆጣጣር መንግሰት ከሚያደረገው ጥረት በተጓዳኝ ከአከባቢው ህብረተሰቡ ጋር በመተባባር በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
አንበጣውን ለመቆጣጠር መንግሰት እያከናወኑ ያለው ስራ ብቻ ማጥፋት ስለማይቻልና በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የከብት መኖም ሆነ ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚደርስ በምንችለው አቅም በባህላዊ መንገድ አንበጣውን ለማባረርና ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።