ቀጥታ፡

የመኪና ታርጋ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የመስጠት የሙከራ ትግበራ በሚቀጥለው ሣምንት ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29/2012 (ኢዜአ) የፍጥነት መገደቢያ የሚገጠምላቸው ተሽከርካሪዎች የመኪና ሰሌዳ (ታርጋ) በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚያገኙበት የሙከራ ትግበራ በሚቀጥለው ሣምንት እንደሚጀመር ተገለጸ።

የሕዝብ ትራንስፖርትና የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች እስከ መስከረም አንድ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲያስገጥሙ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአዲስ አበባ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ የሚገጥሙ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

ፍጥነት ጠብቆ አለማሽከርከር በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ዋንኛ መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

የተሽከርካሪዎችን ፍጥነት መቀነስ ዓላማ ያደረገ የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ስለመግጠምና ስለማስተዳደር የወጣ መመሪያ ከታኅሣሥ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።

በመመሪያው አማካኝነት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ላሟሉ ተቋማት የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ የመግጠም የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ይሰጣል።

በዚሁ መሠረት ባለሥልጣኑ ለ42 ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሰጥቶ እስካሁን 28ቱ ወደ ሥራ ገብተዋል።

የአንሃም ትሬዲኒግ ፒኤልሲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ይታገሱ በቀለ ፈቃድ ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ተቋሙ ሁለት ሺህ ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች መሣሪያውን መግጠሙንና በቀን ለ50 መኪናዎች መሣሪያውን እየገጠመ መሆኑን ተናግረዋል።

በመመሪያው መሠረት የቤት መኪና በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር፣ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በሰዓት 80 ኪሎ ሜትር፣ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች በሰዓት 70 ኪሎ ሜትር የፍጥነት ገደብ መቀመጡን አመልክተዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ላይ ዓለም አቀፍ የአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂፒኤስ) መተከሉንና ተሽከርካሪዎቹ በምን ያህል ፍጥነት እየሄዱና የት አካባቢ እየሄዱ እንዳሉ እንደሚያሳይም አቶ ይታገሱ አስረድተዋል።

በዚሁ አማካኝነት የተቀመጠውን የፍጥነት ገደብ የሚጥሱ ከሆነ መሣሪያው የተሽከርካሪውን የነዳጅ ፍጥነት በመገደብ ወደ ነበረበት ፍጥነት ይመልሰዋል ብለዋል።

የኤቢሲ ፓርትነርስ ፒኤልሲ የፍጥነት መገደቢያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳምሶን ገላጋይ ተሽከርካሪዎች ለምን ፍጥነታችን ተገደበ ብለው ቅሬታ እንደሚያነሱ ገልጸዋል።

ይሁንና የፍጥነት ገደቡ የተቀመጠው በመመሪያው አማካኝነት በመሆኑ ከዚያ ውጪ ማድረግ እንደማይቻል አመልክተዋል።

መሣሪያውን አስመልክቶ ወደ መጀመሪያ አካባቢ የግንዛቤ ክፍተት በሁሉም አካላት ላይ እንደነበረና ያ ግን አሁን እየተሻሻለ መምጣቱንና በቀጣይ የግንዛቤ መፍጠር ሥራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኘው መመሪያው የወጣው በፍጥነት ምክንያት የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ መሆኑን ገልጸዋል።

የፍጥነት መገደቢያ የሚገጠምላቸው ተሽከርካሪዎች ታርጋ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚያገኙበት የሙከራ ትግበራ በሚቀጥለው ሣምንት እንደሚጀመር አመልክተዋል።

አገልግሎቱ በሙከራ ደረጃ ለ10 ቀናት በገላን ደረቅ ወደብ የሚጀመር ሲሆን በትግበራው መሠረት ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባው አስመጪ ተሽከርካሪዎቹን ኦንላይን ይመዘግባል ብለዋል።

በምዝገባው አስመጪውና ፍጥነት መገደቢያ ገጣሚው ተቋም በኦንላይን ውል በማሰር ተሽከርካሪው ከወደብ ሲለቀቅ የመግጠሙን ሥራ እንደሚያከናውኑ ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በሲስተሙ አማካኝነት የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ መገጠሙን አረጋግጦ ፈቃድ በመስጠት በመዲናዋ ለሚገኙት ክፍለ ከተሞች እንደሚያሳወቅ አስረድተዋል።

በክፍለ ከተሞቹ አገልግሎት የሚሰጡት አካላት በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የተከናወኑ ሥራዎችን በሲስተሙ ተመልክተው መሣሪያው የተገጠመለት ተገልጋይ ሲመጣ የመኪና ሰሌዳውን እንደሚያገኝ አመልክተዋል።

የሙከራ ትግበራው ተሞክሮ ተወስዶ አገልግሎቱ ወደ ሙሉ ትግበራ ሊገባ እንደሚችልና ማሻሻያም ካስፈለገ የአሰራር ሥርዓቱ ማሻሻያ እንደሚደረግ አቶ ይግዛው አብራርተዋል።

የፍጥነት መገደቢያ እንዲገጥሙ ፈቃድ ከተሰጣቸው 42 ተቋማት 14ቱ ወደ ሥራ ስላልገቡ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግና ካልሆነም ፈቃዳቸው እንደሚነጠቅ ተናግረዋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በላይ በበኩላቸው የሕዝብ ትራንስፖርትና የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች እስከ መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲያስገጥሙ የጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

በተደጋጋሚ ጥሪ አንደተደረገና በጊዜ ገደቡ የማያስመዘግቡ ተሽከርካሪዎች በመመሪያው መሠረት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አመልክተዋል።

የመንግሥት ተሽከርካሪዎችና የቤት መኪኖች በቀጣይ መሣሪያውን እንዲገጥሙ እንደሚደርግ አሁን ትኩረት የተሰጣቸው ግን ይበልጥ አደጋ አድራሽ በተባሉ የተሽከርካሪ ዓይነቶች ላይ ነው ብለዋል።

እስካሁን መመሪያው ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ 17 ሺህ 258 ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንደተገጠመላቸው አቶ ያዕቆብ አስረድተዋል።

ከውጭ በሚገቡ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ መሣሪያው እየተገጠመላቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።

መሣሪያውን የመግጠም ሥራው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች ሥራው መጀመሩን ገልጸው በሌሎች ክልሎችም ይቀጥላል ብለዋል።

የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ስለመግጠምና ስለማስተዳደር የወጣው መመሪያ በኢትዮጵያ በሚገኙ ሁሉም አሽከርካሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም