ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኤሌክትሮኒክ የአየር ትኬት ክፍያ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2012( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ'' ጉዞ ጎ'' በተሰኘ የኦንላይን መተግበሪያ የኤሌክትሮኒክ የአየር ትኬት ክፍያ ለመጀመር ''ሶልጌት ትራቭል'' ከተባለ የግል ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን እንደገለጹት፣ የአገልግሎቱ መጀመር ደንበኞች የኤሌክትሮኒክ ክፍያ የአየር በረራ ትኬቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

የኤሌክትሮኒክ አሰራሮች  የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በማስቀረት ዓለም ከደረሰበት የባንክ አገልግሎት ጎራ የሚያሰልፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአሁኑ አሰራር ደንበኞች ወደ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሳይሄዱ ባሉበት ሆነው የክፍያ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የ''ሶል ጌት ትራቭል'' ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ስለሺ በበኩላቸው፣ ''የጉዞ ጎ ''የኦንላይን መተግበሪያ ለደንበኞች ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።

ደንበኞች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ አየር መንገዶችን በተለያዩ መመዘኛዎች በመፈተሽ የተሻለውን እንዲመርጡ የሚያስችላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

መተግበሪያው ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ተጓዥች የተዘጋጀ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት አኳያም የራሱ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

"የጉዞ ጎ "መተግበሪያ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የሚሰራ ሲሆን በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ ፣በትግርኛ፣ በሶማልኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሚተገበር ነው።

ስማርት ሞባይል ተጠቃሚ ያልሆኑ ደንበኞችም 74 73 ላይ በመደወል ለጉዞ ቦታ ለማስያዝ መመዝገብ ይቻላሉ ተብሏል።

ደንበኞች በአቅራቢያው በሚገኝ በየትኛውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርጫፍ በመገኘት የሚሄዱበትን አገር ፣መጓዝ የሚፈልጉበትን የበረራ አይነትና የጉዞውን ቀን በማሳወቅ 5 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መስተናገድ ይችላሉ ተብሏል።

ክፍያውን  በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ብር እና በሲቢኢ ብር ወኪሎች እንዲሁም በመደበኛው የባንኩ ቅርጫፍ መስኮቶች መፈፀም ይቻላል።

ደንበኞች ከሂሳባቸው ተቀናሽ በማድረግ ወይም በካሽ ክፍያ በመፈጸም የአየር ቲኬት ሽያጭ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም