ቀጥታ፡

በደቡባዊ ትግራይ በአንበጣ የወደሙ ማሣዎች ፈጥኖ በሚደርሱ ሰብሎች እየተሸፈኑ ነው - የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ

ይጨው፣ ነሐሴ 29/2012 (ኢዜአ)  በትግራይ ደቡባዊ ዞን በአንበጣ መንጋ ጉዳት የደረሰባቸው ማሣዎችን በቶሎ በሚደርሱ ሰብሎች መልሶ ለመሸፈን የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ኃይለ ታደለ ለኢዜኣ እንደገለጹት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በዞኑ በሦስት ወረዳዎች በሚገኙ 21 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋ ተከስቶ በሰብሎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

አንበጣው በ12 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተሸፍኖ ከነበረው ሰብል መካከል በሁለት ሺህ ሄክታር ላይ የለማ የጤፍ፣ ስንዴና ገብስ ሰብሎች ጉዳት ማድረሱን ኃላፊው ተናግረዋል።

የሦስት ሺህ ኣርሶ አደሮችን ማሣ ከቀላል እስከ ከባድ የደረሰ ውድመት ማስከተሉን ጠቅሰው እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ሙሉ በሙሉ የወደመውን ሰብል ፈጥኖ በሚደርሱ ሌሎች ሰብሎች የመተካት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ኃይለ ተናግረዋል።

"የትኛውም ማሣ ጦም ማደር ስለሌበት ከየአከባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ሁሉም ቶሎ በሚደርሱ ሰብሎች እንዲሸፈኑ ይደረጋል" ብልዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው አርሶ አደሮችም የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በመስጠት በመስኖ ልማት ጭምር ማሣዎቻቸው እንዲለሙ እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው አስታውቀዋል።

ወደ ዞኑ ከገባው የአንበጣ መንጋ 60 በመቶ ያህሉ ወደ ሌሎች የክልሉ ዞኖች እንዳይስፋፋ በኬሚካልና በሰው ኃይል እንዲጠፋ መደረጉን ገልጸው በቀጣዮቹ ወራት ሊከሰት የሚችለውንም ለመከላከል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከሁለት ሣምንታት በፊት አንድ ሄክታር በሚጠጋ የጤፍ ማሣቸው ላይ ያረፈው የአንበጣ መንጋ ሰብላቸውን በማውደሙ ለችግር መጋለጣቸውን ያስታወሱት ደግሞ በዞኑ የራያ አዘቦ ወረዳ ካራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኃይሉ ዳውድ ናቸው።

በአንበጣው የደረሰባቸውን ጉዳት ለማካካስና ማሣቸው ጦሙን እንዳያድር የቻሉትን ያክል እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸው መንግሥት ኣስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማይ ዘውዱ በበኩላቸው ሩብ ሄክታር የጤፍ ማሣቸው በአንበጣ ሙሉ በሙሉ ቢወድምባቸውም በባለሙያዎች እገዛ መሬታቸውን እንደገና ለማልማት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀምም ያጋጠማቸውን ጉዳት ማካካስ እንዲችሉ የሚደረግላቸው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም