ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የኤርትራ ኤምባሲ ሊከፈት ነው

አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2010 በአዲስ አበባ የኤርትራ ኤምባሲ ሊከፈት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ገለጹ። ሚኒስትሩ እንዳሉት፤  በኢትዮጵያ ያለው የኤርትራ ኤምባሲ የማደስ ሥራው ተጠናቆ ይፋዊ የመክፈኛ ሥነ-ሥርዓት ነገ ወይም ከነገ በስቲያ ይካሄዳል። ኤምባሲው የሚከፈተው የኤርትራ ልዑካን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የደረሱትን ሥምምነት ተከትሎ መሆኑንም ነው የገለጹት። በቅርቡም ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በአስመራ እንደምትከፍት ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከቀናት በኋላ ወደ አስመራ የቀጥታ በራራ ይጀምራል ብለዋል። ሌሎችም ተመሳሳይ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በማከናወን የአገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት የተሳለጠ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ከዛ ባለፈ አገራቱ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በመቋቋም በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የትብብር መስክ ዳግም ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ። አገራቱ በአሁኑ ወቅት የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመራቸውን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም