ቀጥታ፡

ስልጠናው የብልጽግናን ቀጣይ ተልዕኮዎች የሚያስፈጽም አመራር ለማዘጋጀት አግዟል

ባህር ዳር ፣ነሐሴ 29/2012 (ኢዜአ) በብልጽግና እሳቤዎች ቀጣይ ተልዕኮዎችን የሚያፈጽም አመራር ለማዘጋጀት ስልጠናው ማገዙን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ለክልሉ የፓርቲው አመራሮች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

የስልጠናውን መጠናቀቅ አስመልክተው የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት የስልጠናው ዓላማ የአመራሩን አቅም ማሳደግና ለቀጣይ ተልዕኮዎች ለማዘጋጀት ነው።

የብልጽግና እሳቤዎችን የማስረጽ፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችና ሌሎች ጉዳዮችን በመዳሰስ እውቀትና ክህሎትን በመገንባት ላይ ስልጠናው አተኩሮ ተካሂዷል ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጡ የመጣበትን መንገድ፣ አሁን ላይ የደረሰበትን እድገትና ያጋጠሙት ፈተናዎች እንዲሁም በቀጣይ መከናወን ባለባቸው ተግባራት ላይ መግባባት መደረሱን  ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ በኋላ የኮሮና ቫይረስን በመከላከል፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መካሄዱና ሌሎችም የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት በስልጠናው መወሳቱን   አቶ አገኘሁ አስረድተዋል።

በቀጣይ በከተሞች መሰረተ ልማት፣ ኢንቨስትመንትና ግብርና ልማት ላይ በማተኮር ለወጣቱ  የስራ እድል ፈጠራና ገቢን ማመንጨት የሞት ሽረት ተግባር መሆኑን መግባባት ተችሏል ብለዋል።

ከኮሮና ክስተት  በኋላ ሊፈጠር የሚችል የምግብ እጥረትን ለማስወገድ  የግብርና ልማትና በሽታውን  መከላከል ላይ በትኩረት ካልተሰራ ክልሉንም ሆነ ሀገሪቱን ዋጋ እንደሚያስከፍል መግባባት ተደርሷል።

አሁን ክልሉ ያለበትን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ በማስገንዘብ በቀጣይ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ዘላቂነት ያለው ስራ ለማከናወን መነሳሳት የፈጠረ ነው ብለዋል።

በተለይም የተዘበራረቀውን የአመራሩን አስተሳሰብና አመለካከት በቡድን ውይይትና በጋራ መድረክ በመታገዝ በተካሄደው ስልጠና ወደ አንድነት በማምጣት ለቀጣይ ተልዕኮ  ያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ አመራሮችም ወደየአካበቢያቸው ሲመለሱ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች  በተፈጠረላቸው አቅም ተጠቅመው ለመመለስ እንደሚሰሩ መግባባት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።

በአዲሱ ዓመት ኮሮና  በትምህርት አጀማመር፣ ገበታ ለሃገር የጎርጎራ ፕሮጀክት ለክልሉ ያለውን ፋይዳ በተመለከተ  ነገ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም