በኢትዮጵያ ከ760 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመጤ አረም ተወሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከ760 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመጤ አረም ተወሯል
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 29/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እስካሁን ከ760 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመጤ አረም መወረሩን የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። አረሙን በዘላቂነት ለመከላከል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የሚያስፈልግ መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የእምቦጭ አረምን ጨምሮ ከ30 በላይ የተለያዩ መጤ የአረም ዝርያዎች በስፋት በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የጣና ሃይቅ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የእምቦጭ አረም እየተስፋፋበት ይገኛል።
አረሙን ለማስወገድ በማሽን፣ በሰው ጉልበት፣ በነፍሳት እንዲሁም በኬሚካል ጥረት ቢደረግም እስካሁን የተሳካ ውጤት አልተገኘም።
አረሙ አሁንም ለጣና ከፍተኛ ስጋት ሆኖ የቀጠለ ሲሆን 130 ኪሎ ሜትር በላይ የሐይቁ ዳርቻ በእምቦጭ እንደተሸፈነ ይገመታል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የመጤ አረም መስፋፋት በተለይ በሰብል ምርት መቀነስ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያስከተለ መሆኑ ይነገራል።
አረሙ በዓሳ ሃብትና ብዝኃ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደረም ይገኛል።
እስካሁን በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከ760 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመጤ አረም መወረሩም ታውቋል።
በኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት የጄኔቲክ ሀብት ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በቀለ እንደሚሉት የመጤ አረሞች መስፋፋትና ተፅእኖ እየበረታ መጥቷል።
አረሙ በብዝኃ ህይወትም ሆነ በአካባቢያዊ ስነ-ምህዳር ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑንም ገልጸዋል።
አረሙን በዘላቂነት ለመከላከል ራሱን የቻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ ባለመኖሩ የእስካሁኑን የመከላከል ሂደት ውጤታማ እንዳላደረገውም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የመጤ አረም መከላከል ፖሊሲ ማዘጋጀት፣ተቋም መገንባት እና በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ35 የሚልቁ መጤ የአረም ዝርያዎች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።