ቀጥታ፡

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት የ'ትውልድ ለሰላም' መርሃ ግብርን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29/2012 (ኢዜአ) የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የ'ትውልድ ለሰላም' መርሐ ግብር አካል የሆነውን 'የአንድ ሚሊዮን ዜጎች የፊርማ ማኖር' ዘመቻ በይፋ አስጀመሩ።

'የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድምፅ ለሰላም' በሚል መሪ ሀሳብ በስድስት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተመሠረተው የ'ትውልድ ለሰላም' ኢንሸቲቭ ሕዝብ ተኮር የሆነ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ ንቀናቄ ነው።

በዛሬው ዕለትም ኢኒሼቲቩን የሚደግፉ ሰዎች የሚፈርሙበት 'የአንድ ሚሊዮን ፌርማዎች ዘመቻ' በይፋ ተጀምሯል።

ቀዳሚውን ፊርማም የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዛሬው ዕለት አስቀምጠዋል።

'የአንድ ሚሊዮን ፊርማዎች ለሰላም' ንቅናቄም ለቀጣይ ሦስት ወራት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ይካሄዳል።

የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ወጣት ሣሮን ልሣነወርቅ በሰጠችው መግለጫ 'ትውልድ ለሰላም' በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ባሉ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በርካታ ፕሮጀክቶችን ያቀፈ ነው።

በፕሮግራሞችም መተማመን መፍጠር፣ ልዩነቶችን በሰላም መፍታትና የሻከሩ ግንኙነቶችን ማስወገድ በአጠቃላይ ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማምጣት ኅብረተሰቡ ለሰላም ግንባታ ሚናው እንዲጎላ ያደርጋል።

የመርሐ ግብሩ ራዕይም "ጠንካራ፣ ሰላማዊና ልዩነቶችን በውይይትና በምክክር የሚፈታ ትውልድ መፍጠር" መሆኑንም ገልጻለች።

ለዚህም ሁሎም ለሰላም ግንባታ የድርሻቸውን የሚያበረክትበት መድረክ በመፍጠር ለዘላቂ ሰላም መሠረት እንዲጣል ተልዕኮ እንዳለው አብራርታለች።

የኢኒሼቲቩ ፕሮፖዛልም ከግማሽ ዓመት በፊት ለሰላም ሚኒስትር ቀርቦ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ለግጭት መንስኤዎችና መፍትሔዎች የሚሆኑ የተለያዩ ጥናታዊ ሥራዎችም ይከናወናሉ ብላለች።

የጥናት ውጤቶችም ለፖለቲካ ልሂቃን፣ ለሕዝብና ለመንግሥት ቀርበው ምክክር የሚደረግባቸው መሆኑን ገልጻለች።

ኢኒሼቲቩ ከማንኛውም ሃይማኖት፣ ብሔርና የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ለኢትዮጵያ የጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማምጣት እንደሚሰራ ገልጻ፤ ለዚሁ አጋርነት ከሃይማኖት፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ሲቪክ ማኅበራት ጋር በጋራ ይሰራል ተብሏል።

ለቀጣይ ዘጠኝ ወራት የሚቆየው የ'ትውልድ ለሰላም' ንቅናቄ የአንድ ሚሊዮን ፊርማዎችን ማሰባሰብ ዘመቻን ጨምሮ ሌሎች ፕሮግራሞች ይኖሩታል።

በመሆኑም ሁሉም ዜጋ የንቅናቄው አካል በመሆን በአካልም ሆነ በኢንተርኔት በሚደረገው የፊርማ ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት ለሰላም ፊርማውን እንዲያስቀምጥ ጠይቀዋል።

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ የሰላም ችግር ትናንት ያደሩ የፍትሕ፣ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ድርብርብ ችግሮች ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ላለፉት 50 ዓመታት የነበረው ደካማና ያልሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ለአሁናዊ ሁለንተናዊ ሰላም እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፤ ችግሩ ለነገው ትውልድ እንዳይሻገር በዚህ ትውልድ ላይ መሠረት መጣል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለቀጣይ ትውልድ መፃዒ ዕድል የሚውል የተስተካከለ መሠረት በመጣል በትውልድ ቅብብሎሽ ለማስቀጠል ይህ የሰላም ኢንሸቲቩ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የትውልድ ግንባታ መሠረት ደግሞ ከቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤትና ከማኅበረሰብ ተነስቶ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ሰላምን በትውልድ ላይ ለመትከልና ለማስረጽ ስትራቴጂ መንደፉን የገለጹት ሚኒስትሯ የ'ትውልድ ለሰላም' ንቅናቄም የስትራቴጂው አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህም በሰላም ጉዳይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ሁሉም ዜጋ የሰላም ንቅናቄው አካል እንዲሆን ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም በበኩላችው ይህ ትውልድ አገርን ሰርቶ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከኪነ ጥበብ፣ ከባህልና ከአጠቃላይ የማኅበረሰቡ እሴቶች የተፋታ መሆኑን ገልጸው፤ በሁሉም መስክ የተሰማራ ባለሙያ በጋራ ሠርቶ የተፈጠረውን ክፍተት መሙላት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ይህ ትውልድ የትናንትን ዋጋ መክፈል ሳይሆን ከትናንት መማር፣ ዛሬን ማበጀትና ለቀጣይ ትውልድ ደግሞ የማቀበል ተራማጅ እሳቤ ሊይዝ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱም ከትውልድ ለሰላም ንቅናቄ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም