በአሶሳ ኮሮናን በመከላከሉ በኩል የሚስተዋለው መዘናጋት እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአሶሳ ኮሮናን በመከላከሉ በኩል የሚስተዋለው መዘናጋት እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች ገለጸ
አሶሳ፣ ነሐሴ 29 / 2012(ኢዜአ) በአሶሳ ከተማ ኮሮናን ለመከላከል ይደረግ የነበረው ጥረት አሁን ላይ የሚስተዋለው መዘናጋት እንዳሳሰባቸው በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከነዋሪዎች መካከል አዲስ በተዘጋጀው የግብይት ስፍራ ብቻቸውን ሸቀጥ ዘርግተው ለመሸጥ ገዥ በመጠባበቅ ላይ የነበሩት አቶ ፈንታው የማታው እንዳሉት የገበያው ቦታ ከወራት በፊት ሶስት ቦታ እንዲከፈል ተደርጓል፡፡
ገበያው ህብረተሰቡ አካላዊ ርቀቱን በመጠበቅ የቫይረሱን ስርጭት እንዲቆም መዘጋጀቱ መልካም የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የግብይት ስፍራው ከዚህ ቀደም ወደ ነበረበት አንድ ቦታ መመለሱን ተናግረዋል፡፡
"ህብረተሰቡ የበሽታውን ጉዳት በሚገባ የተገነዘበ አይመስለኝም " ያሉት አቶ ፈንታው በዚህም የሚስተዋለው ቸልተኝነትና መዘናጋት አሳሳቢ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የድርሻቸውን ለመወጣት በማሰብ ብቻቸውን አዲስ ከተዘጋጀው ቦታ ግብይት ለማካሄድ መወሰናቸውን አስተያየት ሰጪው ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ዘምዘም ሙክታር በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በአንድ መናኸሪያ የሚታየውን መጨናቅ ለማስቀረት የተወሰደ መፍትሔ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን እየተነገረ ባለበት ወቅት ህብረተሰቡ አማራጭ ቦታዎችን ከመጠቀም ይልቅ ለቫይረሱ በሚያጋልጥ መልኩ በቀድሞው መናኸሪያ መመለሱ የሚያሰጋና አሳሰቢ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪ በተዘጋጀው የግብይት ስራፍም የሚጠቀም የለም ብለዋል፡፡
መንግስት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃፊነት ቢኖርበትም ህብረተሰቡ ለራሱ ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የአሶሳ ከተማ የሃገር ሽማግሌ ሃጂ ከድር አልከሪም ናቸው፡፡
የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት በከተማው ጭንብል መጠቀምና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ መዘናጋቱን ታዝበዋል።
ራስን ከቫይረሱ ለመከላከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭብል ማድረግ፣ ርቀትን መጨበቅ መሠረታዊ ጥንቃቄዎች ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ስለሆነ ተግባራዊ ማድረግ አለብን አለብን ብለዋል፡፡
የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የአሶሳ ከተማ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አንዋር ያሲን በበኩላቸው በከተማው የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን መስዋዕትነት በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለማቆም ቤት ለቤት ጭምር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማው አውቶቡስ ተራ ያለው የህዝብ መጨናነቅ ማስተካከል ያልተቻለው በግብረ ኃይል በኩል የቅንጅት ክፍተት በመኖሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ ህዝብ በብዛት የሚጠቀምባቸውን የመንግስት እና የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ከአገልግሎት በፊት በጸረ-ተህዋሲ መደኃኒት መርጨትን ጨምሮ የተጠናከረ መከላከል ስራ እንደሚቀጥል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የግብረ ኃይሉ አባልና የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ምክትል ኢንስፔክተር ደረጀ ኢታና በአሶሳ ኮሮናን ለመከላከል ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ በከተማው አውቶቢስ ተራ፣ የግብይት እና የጫት መሸጫ ቦታዎች ፈታኝ ሁኔታቸው እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
በከተማው ተጨማሪ ሶስት አዳዲስ የግብይት ቦታ ለማስጀመር የተደረገ ጥረት ቢኖርም ህብረተሰቡ የሚፈለገውን ሸቀጣ ሸቀጥ አናገኝበትም ነጋዴው ደግሞ ገዥ አጣን በሚል መቅረቱን ገልጸዋል፡፡
በህብረተሰቡ ላይ ጫና ላለመፍጠር በአንድ የግብይት ቦታ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲገበያይ ለማድረግ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ከሚመከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተጨማሪ የግብይት ቦታዎችን እና አውቶቡስ መናኸሪያዎች ስራ ማስጀመር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡