ጳጉሜን አንድ የሳይክልና የእግረኞች ቀን ሆኖ እንደሚከበር ተገለጸ

86

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29/2012(ኢዜአ) ጳጉሜን አንድ የሳይክል እና የእግረኞች ቀን ሆኖ እንደሚከበር የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ጸጋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቀኑ በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም አካባቢዎች ይከበራል።

"በዕለቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከለቡ እስከ ጀሞ ባለው የብስክሌት መንገድ ላይ በመጪው እሁድ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት እስከ 3:30 ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሳይክል በመንዳትና በተለያዩ መርሃግብሮች እንደሚከበር ተናግረዋል።


ቀኑ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ገልጸው ይህም ሰዎች ሳይክልን፣ በእግር መጓዝና ሌሎች ሞተር አልባ የትራንስፖርት አማራጮችን እንዲጠቀሙ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው በተባለው ቀንና ሰዓት ላይ ለሞተር ትራንፖርት ዝግ እንደሚሆን ያመለከቱት አቶ እንዳልካቸው ዓመቱን ሙሉ ወር በገባ በመጨረሻው እሁድም እንደሚከናወን ተናግረዋል።
 
በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች የተለመደው የሞተር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንደሚቀጥልና ምንም አይነት ክልከላ በሞተር ትራንፖርት ላይ አለመኖሩን ተናግረዋል።

አቶ እንዳልካቸው እንዳሉት በእግር እና በብስክሌት የሚደረጉ ጉዞዎች የሞተር አልባ ትራንስፖርት በመሆናቸው የትራፊክ መጨናነቅና አደጋዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጾ ይኖራቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሞተር አልባ ትራንስፖርት የአየር ብክለት ችግሮችን ለመቀነስና የማህበረሰቡ ጤናም እንዲጠበቅ ተመራጭ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም